ቀጥታ፡

ውህደቱ ወቅታዊና ሃገሪቱ ለደረሰችበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስፈላጊ ነው....የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

መስከረም 24/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አበዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር ውህደት ወቅታዊና ሃገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስፈላጊ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። አሁን ያለው የግንባርና የአጋር አደረጃጀት ሁለት ዓይነት ዜግነትን መፍጠሩንም ምሁራኑ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ትምህርት ክፍል የፖለቲካል ኢኮኖሚ መምህሩ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ እንደገለጹት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለው የግንባርና አጋር አደረጃጀት የዜጎችን የፖለቲካ በእኩል የማያስተናግድ ነው። “በዚህም አጋር ድርጅቶች ሃገር የመምራት እድሉም አቅሙም እንዳይኖራቸው ከማድረጉ ባለፈ በብሄራዊ ድርጅቶች መካከልም እኩል ተሳትፎ አልነበረም” ብለዋል፡፡ ዶክተር የሺጥላ እንደሚሉት ኢህአዴግ ወደ ውህደት መምጣቱ የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት በሃገሪቱ ያሉ ዜጎችን አሳታፊ በማድረግ ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ኢህአዴግን ጨምሮ በርካቶቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ማንነትን መሰረት አድርጎ መመስረታቸውና የፌዴራለዚም ስርዓቱም ይህንኑ ማንጻባረቁ በአንዳንድ ሊህቃን ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ “ይሁን እንጂ ውህደቱ የዜጎችን መብት የሚጨፈልቅ ሳይሆን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው” ብለዋል፡፡ “የመንግስት አወቃቀር ሳይሆን የምንከተለው የፖለቲካ ስርዓት ነው ቀውስ ሊፈጥር የሚችለው” የሚሉት ዶክተር የሺጥላ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተፈጠረውን ቀውስ በማሳያነት በመጥቀስ የውህደቱን ጠቃሚነት ተናግረዋል። ውህደቱ በፌዴራል ስርዓቱ አተገባበር ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት አሁን ሃገሪቱ ለሚያስፈልጋት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው። “ለውህደቱ ውጤታማነት አጋርና የግንባሩ አባል ድርጅቶች የህልውና ጉዳያቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል” ያሉት መምህሩ “ፖለቲካ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ውህደት በመፍጠር አንድ ሃገር መገንባት አለባቸው” ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የከተማ ልማት ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪው ዶክተር ኢንጂነር እሸትአየሁ ክንፉ በበኩላቸው “ለሩብ ምዕተ ዓመት የተከተልነውን የፌደራል ስርዓት ለማሳደግ የኢህአዴግ ውህደት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡ የርዕዮተ አለም፤ የአደረጃጀትና የፍልስፍና ልዩነት በሌላቸው ፓርቲዎች መካከል ልዩነት መፈጠር የለበትም የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው የከተሞችን እድገት ጥያቄ በክልል ፌደራሊዝም መመለስ አይቻልም ይላሉ፡፡     “የምንከተለው ፌዴራሊዝም በሽግግሩ ወቅት ካለንበት ችግር አሻግሮን ነበር” ያሉት ዶክተሩ የስርዓቱ አለመዳበር አጋር የምንላቸውን ድርጅቶች ያገለለና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያላረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   ምሁራኑ እንደሚሉት ውህደቱ ወደ አሃዳዊነት ይወስደናል በሚል የግንዛቤ እጥረት በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚተላለፉ መረጃዎች ተገቢነት ስሌላቸው ሃላፊነት የሚሰማቸው መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም