የኢሬቻ ታዳሚዎች በአዲስ አበባ ነዋሪዎች አቀባበል ተደስተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ ታዳሚዎች በአዲስ አበባ ነዋሪዎች አቀባበል ተደስተዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መስከረም 24 ቀን 2012 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢሬቻ በዓል ታዳሚ እንግዶች ያሳዩት ፍቅር የተሞላበት መስተንግዶ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ተባለ። በአዲስ አበባ ከ150 ዓመታት በኋላ በተከበረው የኢሬቻ በዓል አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናትና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና እንግዶች ታድመዋል። ከታዳሚያኑ መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን ተሰጡ እንግዶች እንዳሉት የአዲስ አበባ ነዋሪ ከየአቅጣጫው ለመጣው ህዝብ ያደረገው አቀባበል የሚደነቅ ነው፤ ሊመሰገንም ይገባል። ለኢሬቻ ታዳሚያን ምግብና ውሃ ከማቅረብ ባሻገር ነዋሪዎቹ ባሳዩት ፍቅር የተሞላበት መስተንግዶ በእጅጉ መደሰታቸውንም ገልጸዋል። ከአዳማ የመጣው ወጣት ሃሰን ያዕቆብ እና ከሰበታ የመጣው ወጣት ቢሊሴ መገርሳ ኢትዮጵያዊያን የአንድ እናትና አባት ልጆች በመሆናችን በመከባበርና በመተባበር አገራችንን ልንገነባ ይገባልም ነው ያሉት። ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም የበዓሉ ታዳሚ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል። የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በመጀመሪያ ሠላም፣ ፍቅርና መከባበር ሊኖር ግድ ይላል የሚሉት የበዓሉ ታዳሚያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ወደፊት 'ልንጓዝ ይገባል' ብለዋል። የኦሮሞና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀው በዓሉን አድምቀውታል።