አብሮነታችንን የማይሹ ኃይሎችን በጋራ መከላከል ይገባል - አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነታችንን የማይሹ ኃይሎችን በጋራ መከላከል ይገባል - አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 24/2012 የኢትዮጵያዊያንን አብሮነትና መተባበር የማይሹ ኃይሎችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ በኢሬቻ በዓል የታደሙ አባ ገዳዎች፣ ፎሌዎችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ። የበዓሉ ታዳሚዎች የሆኑት አባገዳዎች፣ ፎሌዎችና የአገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ከጥንትም ተዋህደው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ሆኖም አሁን አሁን የአገር ፍቅር የሌላቸው አካላት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ዘመናትን በአብሮነት የተሻገረውን ህዝብ ለማጋጨት ሲታትሩ ይስተዋላል። አብዛኛው ህዝብ ዛሬም ድረስ አብሮነቱና መተባበሩ እንደቀጠለ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አብሮነትና መተባበራችንን የማይሹ ኃይሎችን በጋራ 'ልንከላከላቸው ይገባል' ይላሉ። የኦሮሞ ህዝብ በገዳ-ስርዓት የሚጠቀምበት ጉዲፈቻ ከሌሎች ጋር በመቀራረብ ለመኖር ትልቅ ማስተማሪያ እንደሆነ በማንሳትም እንዲህ ያለውን ባህል ልንጋራው ይገባል ብለዋል። ከምዕራብ ሸዋ የመጡት አባጋዳ ታከለ ዲንሳ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖር የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ጋር በመከባበርና በመተሳሰብ ይኖርበት የነበረው እሳቤ ዛሬም ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል። ከምስራቁ የአገሪቷ ክፍል ድሬዳዋ የመጡት አቶ አቢቲ አብዱራህማን በበኩላቸው የሚኖሩበት አካባቢ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስተሳስር መሆኑን በመጥቀስ ይህን በአርዓያነት በመውሰድ ዛሬም ለአንድ አገር ግንባታ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በዓሉን ስናከብር በመተባበርና በጋራ እንደሆነው ሁሉ በአገር ግንባታውም አንድነታችንን በማስተጋባት ሊሆን ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።