ኤልያስ መልካ እና የሙዚቃ ህይወቱ - ኢዜአ አማርኛ
ኤልያስ መልካ እና የሙዚቃ ህይወቱ

መስከረም 24/2012.. ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ ባደረበት ህመም ትናንት ሌለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከሙዚቃ አቀናባሪነቱ ሻገር ጊታሪስት፣ ገጣሚና የዜማ ደራሲው ኤሊያስ መልካ ትናንት ሌሊት ህይወቱ ማለፉን የሰሙ ጥልቅ ሀዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው። ኤሊያስ በስኳር ህመም ሲሰቃይ መቆየቱ ይነገራል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ኩላሊቱ መስራት አቁሞ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ይገልጻሉ። እድሜው በ40ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሆነው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ የተወለደው አብነት አዲስ ከተማ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሃይሉ ተስፋዬ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከፍተኛ ሰባት ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በየካቲት 2011 ዓ.ም በፋና ቴሌቪዥን ፋና ቀለማት ፕሮግራም "ሙዚቃን የኖረው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ" በሚል የቀረበው ዶክመንተሪ ኤሊያስ በትምህርቱ በጣም ጎበዝና ታታሪ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ኤሊያስ መልካ ወደ ሙዚቃ ህይወት ከመግባቱ በፊት በጣም ጎበዝ ኳስ ተጫዋች እንደነበረም ወዳጆቹ እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። ቁመቱ አጭር በመሆኑ ጓደኞቹ "ትንሹ ማራዶና" በሚል ቅጽል ስም እንደሚጠሩትም ይነገራል። ባለው የኳስ ጨዋታ ክህሎትም ኤሊያስ ወደ ፊት ጥሩ ኳስ ተጫዋች እንጂ ሙዚቀኛ ይሆናል ብሎ የጠበቀ እንዳልነበር ጓደኞቹ ይገልጻሉ። ኤሊያስ መልካ በልጅነቱ የቀለም ቆሮቆሮዎችን ሰብስቦ በእንጨት በመምታት የሚያወጣቸው ድምጾች በጣም ያስገርማቸው እንደነበርም ነው ጓደኞቹ የሚናገሩት። ኤሊያስ መልካ በ1987 ዓ.ም ወደ ያሬድ ሙዚቃ ቤት በመግባት ተምሮ ቼሎና ሊድ ጊታር ይጫወት ነበር። ከሙዚቃ መምህራኑ እዝራ አባተ፣ አክሊሉ ዘውዴ እና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመዲና ባንድ ውስጥ ሰርቷል። ከመዲና ባንድ በተጨማሪ ኤሊያስ በዜማ ላስታስና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች የተጫወተ ሲሆን፤ ከ30 በላይ ሙሉ አልበሞችን አቀናብሯል። ኤሊያስ መልካ ከአለማየሁ እሸቴ፣ ፍቅር አዲስ ነቅዓጥበብ፣ ከአረጋኸኝ ወራሽ፣ ከመሐሙድ አህመድ፣ ከዘሪቱ ከበደ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ኃይሌ ሩትስና ከሌሎች ድምጻዊያንም ጋር ሰርቷል። ከአልበሞች በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሕብረ ዝማሬዎችን ማቀናበሩ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል መላ መላ፣ ማለባበስ ይቅር፣ ለአፍሪካ ሕብረት፣ በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮሩት ይጠቀሳሉ። ከሙዚቃ ማቀናበር ስራው በተጨማሪ በተወሰኑ ኮንሰርቶች ላይ ከባንዶቹ ጋር በመሆን ከታዋቂ ድምጻዊያን ጋር የሰራ ሲሆን፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ከዘሪቱ ከበደ ጋር የሰራው ኮንሰርት በዋንኛነት ይጠቀሳል። በገና ስቱዲዩን በማቋቋም የሙዚቃ ማቀናበር ስራውን የጀመረው ኤሊያስ፤ የሚሰራቸው ስራዎች በጣም ታታሪ ጎበዝ ለሙዚቃ የተሰጠ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ድምጻዊያንና የሙዚቃ አስተማሪዎቹ ይመሰክራሉ። ድምጻዊያን ኤሊያስ የሚሰራቸው የሙዚቃ ስራዎች ማንነቱን ስብዕናውን በጣም እንደሚገልጹና በየጊዜው በዓለም ላይ ካለው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ለውጦች ጋር ራሱን በማማሻልና በማብቃት ሁሌም ሙዚቃ የሚፈልገው ደረጃ ላይ የሚገኝ ከያኒ እንደበርም ከእርሱ ጋር የሰሩ ድምጻዊያን ይገልጻሉ። ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ ሰውን መርዳት የሚወድ፣ ጨዋ፣ ተጫዋችና ተግባቢ፣ ደግና ከራሱ ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድም ጥሩ ስብዕና ያለው እንደሆነም የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ። ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ በተለያዩ ሥራዎቹ የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናን አግኝቷል። ኤልያስ መልካ እስካለፈው ሳምንት ቅዳሜ ድረስ በፋና ላምሮት የድምጻዊያን ተስጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል እንደነበርም ይታወቃል። ትናንት ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የኤልያስ መልካ የቀብር ስነ ስርዓት ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን እንደሚፈፀም ተገልጿል። ከቀብሩ በፊት የስንብትና የሀዘን መግለጫ ስነ-ስርዓት እንደሚዘጋጅም ታውቋል።