ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ሲከናወን የነበረው የተጨማሪ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራ ተቋረጠ

ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 24 ቀን 2012 ደቡብ ወሎ ዞን ያጋጠመውን የኤሌክትሪ ኃይል መቆራረጥና ማነስ ችግር ለመፍታት ሲከናወን የነበረው የተጨማሪ መስመር ዝርጋታ ሥራ መቋረጡን በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ዲስትሪክት አስታወቀ። ሥራው የተቋረጠው ባጋጠመ የደንብ ማስከበር ችግር መሆኑንም ዲስትሪክቱ አመልክቷል። የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ዲስትሪክቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በሥራ ላይ እያለ ከመስመር ዝርጋታና ካሳ ጋር በተያያዘ ያለውን መመሪያ ለመስተዳድሩ ባለማሳወቁ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ተናግሯል። የደሴ ዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያሄጅ አቶ ሀብቱ አበበ እንደገለጹት በደቡብ ወሎ ዞን ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኙ አምስት ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ማነስ ችግር በተደጋጋሚ ይገጥማቸዋል። ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው የአቀስታ፣ ለገሂዳ፣ ወረኢሉ፣ ጃማ እና መካነ ሰላም ወረዳዎች በሚወስደው መስመር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ የኢሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና እጥረት እያጋጠመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለመሀል ሳይንት እና ለአማራ ሳይንት ወረዳዎች የ80 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ ስራ በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ ከአቀስታ-ቡሶ ባለው መስመር ዝርጋታ ላይ የግለሰቦች ዛፍ ባለመቆረጡ ምክንያት ከአምስት ወራት በላይ ስራውን ማቆማቸውን ተናግረዋል። ችግሩን ከክልል እስከ ወረዳ ላሉ ባለድርሻ አካላት ቢያሳውቁም መፍትሄ በማጣታቸው ስራውን በጊዜው ለማጠናቀቅ መቸገራቸውን ነው ያስረዱት። የግለሰቦቹን ዛፍ ያለካሳ ክፍያ ቆርጦ መስመር መዘርጋት በአዋጅና መመሪያ መደንገጉን የጠቆሙት አቶ ሀብቱ  በተለይ የዞኑ መስተዳድር ለችግሩ ፈጥኖ ምላሽ አለመስጠቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ዛፎችን በመቁረጥ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘጋት ሲንቀሳቀሱ ከህብረተሰቡ ተቃውሞና ድብደባ እንደደረሰባቸውም አስረድተዋል። የፍስሃና ጓደኞቹ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ማህበር ሥራ አስኪሄጅ ኢንጂነር ፍስሃ ዳምጤ በበኩላቸው ማህበራቸው ከአቀስታ - ቡሶ 52 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ ሥራውን እየሰራ እንደነበር አስታውሰዋል። "ለጋምቦ ወረዳ ቀበሌ 29 ለመድረስ አንድ ኪሎ ሜትር ብቻ ሲቀረን ግለሰቦች ዛፍ አንቆርጥም በማለታቸው ስራውን ለማቋረጥ ተገደናል" ብለዋል። በእዚህም ለአምስት ወራት ያለስራ ለሠራተኞች ደመወዝ በመክፈል ለኪሳራ መዳረጋቸውን ነው ያመለከቱት፡፡ የለጋምቦ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አባተ አረጋ በበኩላቸው ስለጉዳዩ ተጠይቀው ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሩ የይዞታ ማሳው ላይ ባህር ዛፍ በመትከል እንደሚተዳደር ገልጸዋል። ለሚቆረጠው ዛፍ የተጠየቀውን የአንድ ሚሊዮን ብር ካሳ  አስተዳደሩ በበጀት እጥረት ምክንያት ለመክፈል ፈታኝ እንደሆነበትም ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅት የድርጅቱን መመሪያ ለህብረተሰቡ በማሳወቅና ልማቱ ለህብረተሰቡ ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳት ህግ ማስከበር ስራውን ለማናወን እየተንቀሳቀስን ነው" ብለዋል። "ዲስትሪክቱ  ወደ ስራ ከመግባቱ አስቀድሞም ሆነ በስራ ላይ እያለ መመሪያውን ለመስተዳድሩ ባለማሳወቁ የተፈጠረ ችግር ነው " ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ ናቸው፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት በጥቃቅን ጉዳዮች ህብረተሰቡ የመብራት ተጠቃሚ የማይሆንበት ሁኔታ መፈጠር እንደሌለበት በጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ ችግር ፈጥረው የነበሩት ግለሰቦች ራሳቸው ዛፋቸውን እንዲቆርጡ መወሰኑን አስረድተዋል። "በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የየራሳቸውን ዛፍ ካልቆረጡ በግብረ ኃይል በማሽን እንዲቆረጥ በማድረግ ህግን የማስከበር ስራ ይሰራል" ሲሉም አስታውቀዋል። የመብራት ማከፋፈያው የሚገኘው ከ180 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ በመሆኑ በአዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ቢያንስ በየ60 ኪሎ ሜትር አንድ ማከፋፋያ እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሰይድ አመልክትዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም