ቀጥታ፡

የኢንዶኔዢያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 24/2012 የኢንዶኔዢያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ በስፋት እንዲሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ በኢትዮጵያ የኢንዶኔዢያ አምባሳደር አልቡስራ ባስኑርን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚሁ ወቅትም ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን አንስተው የግንኙነታቸውን አድማስ በማስፋት በሁሉም ዘርፍ በትብብር እንዲሰሩ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች ብለዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ እንደመሆኗ የእስያ ባለኃብቶች ለኢንቨስትመንት በከፍተኛ ቁጥር እየመጡ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። የኢንዶኔዢያ ባለኃብቶችም በኢትዮጵያ ያለውን እድል ተጠቅመው በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሳተፉ ከመጋበዝ አንጻር ከአምባሳደሩ ብዙ እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል። አምባሳደር አልቡስራ ባስኑር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሳተፉ ያሉት ኢንዶኔዢያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ሆኖም በአገራቱ መካከል ካለው አቅም አንጻር በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ገልጸዋል። አምባሳደር ባስኑር አክለው በቅርቡ በኢንዶኔዢያ በሚካሄደው ታላቅ የንግድ ኤግዚቢሽን ላይ በርካታ ኢትዮጵያውን ነጋዴዎች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በተካሄደው 74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ተጠቃሚዎች ያለ ቪዛ መግቢያ ስምምነት እንዲሁም በሰላም ማስከበር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1961 ሲሆን ኢንዶኒዢያ በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1964፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በ2016 በኢንዶኔዢያ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል። ኢትዮጵያ የቅባት እህሎች፣ ቡና ሻይ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና ቅመማ ቅመሞችን ወደኢንዶኒዢያ ስትልክ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ ሳሙና፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና የኬሚካል ውጤቶችን በዋንኛነት ታስገባለች። ኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት በባህልና በፖለቲካ መስክ ያላቸው ግንኙነት እያደገ ቢመጣም በንግዱ መስክ ግን የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። በኢትዮጵያ የኢንዶኔዢያ አምባሳደር አልቡስራ ባስኑር በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢንዶኔዢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ በትኩረት እንደምትሰራ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም