ቀጥታ፡

በአንድነት ሆነን የዛሬን ነጻነት እንዳመጣን ሁሉ በጋራ ሆነን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች አገር እንገነባለን---ኢንጅነር ታከለ ኡማ

መስከረም 23/12 ዓ ም በአንድነት ሆነን የዛሬን ነጻነት እንዳመጣን ሁሉ በጋራ ሆነን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች አገር እንገነባለን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። ምክትል ከንቲባው የሆራ ፊንፊኔ በዓል ለማክበር የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። ነገ ከማለዳው 12፡00 ሠዓት ጀምሮ በሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም እንግዶች በአምስቱም በሮች ወደ መዲናዋ መግባት ጀምረዋል። እንግዶቹ በአዲስ አበባ አስተዳደር ክፍለ ከተሞች ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸውም ነው። በመስቀል አዳባባይ በተካሄደው የዋዜማ ስነስርዓት ላይም የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ እንዳሉት "የገዳ ስርዓት አሳታፊነትና አቃፊነትን ባሳየን በኢሬቻ በዓል እንደዚህ አምሮብን እንድንታይ ላደረጉንና ለታገሉት ወንድም እህቶቻችን ምስጋና ይገባቸዋል"። "የጎንደር ልጆች፤ የጎጃም ልጆች፤ የኢትዮጵያ ልጆች፤ የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነው ብለው፤ የሐዋሳ ልጆች፤ የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነው ብለው፣ የራያ ልጆች የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነው ብለው አብረውን ባይታገሉ ኖሮ ዛሬ ኢሬቻን እዚህ ባላከበርን ነበር " በማለትም ነው ምክትል ከንቲባው የገለጹት። የገዳ ስርዓት መገለጫ የሆነውን ኢሬቻን እና ሌሎች ውብ ባህሎቻችንን በማሳደግ አገራችንን ለዓለም ብርሃን ሆና እንዲትታይ እናደጋለን ሲሉም ተናግረዋል። "አሁን የቆምንባት አዳባባይ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወገኖቻችን ሲደበደቡበትና ሲገረፉበት የነበረ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ አሁን ግን ያንን አስከፊ ስርዓት በአንድነት ሆነን እንዳስወገድን ሁሉ በጋራ ሆነን ትውልድን እናሻግራለን፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች አገርም እንገነባለን ብለዋል። በዓሉን ለማክበር የኦሮሚያና ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም የጎረቤት አገራት ዜጎችም እንኳን ወደ መዲናችን ደህና መጣችሁም ብለዋል ኢንጅነር ታከለ። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ዛሬ የተገኘው የድል ብርሃን ለችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። በዓሉን ለመታደም ላመጡት ለመላው ብሄር ብሄረሰቦችና የውጭ እንግዶች "አብራችሁን ቆማችሁ ስላሳመራችሁን ትልቅ አክብሮት አለን" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ነገና ከነገ ወዲያ የሚከበረው ኢሬቻ በዓልም በዚሁ ባማረ ሁኔታና  በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የበዓሉን ወግና ስርዓት ተከትለን ማክበር አለብን ብለዋል። አባ ገዳ ጎበና ሆላ እዚህ ላደረሰን ፈጣሪ ታላቅ ምስጋና ይገባል በማለት ለመላው የበዓሉ ታዳሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። በመስቀል አደባባይ እየተከናወነ ባለው የኢሬቻ በዓል የዋዜማ ስነስርዓት የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ፈረስ ግልቢያ፣ የኦሮሚያ ዞኖች የባህል ትርዒት፣ የባህል ምግቦች ትርዒት እንዲሁም የኢሬቻ የህጻናት መዝሙር ቀርበዋል። በዋዜማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ፎሌዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እንዲሁም ከሀገር ውጭና ከመላው የአገሪቷ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች ታድመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም