የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዳያስፖራ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ቅርንጫፍ ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዳያስፖራ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ቅርንጫፍ ከፈተ
አዲስ አበባ መስከረም 23/2012 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ከፍቶ ስራ ጀመረ። በአዲስ አበባ ለጋሃር አካባቢ የተከፈተው ቅርንጫፍ የባንኩ ፕሬዝዳንት በተገኙበት በዛሬው እለት ስራውን በይፋ ጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና በእለቱ ባደረጉት ንግግር ለዳያስፖራዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ መከፈቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ሁለንተናዊ ልማት እንዲሳተፉ ያደርጋቸዋል ብለዋል። የባንኩ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ዳያስፖራዎች በያሉባቸው አገራት ሆነው በኢትዮጵያ ኢምባሲና ቆንፅላ ፅህፈት ቤት በኩል እንዲገለገሉ ተመቻችቷል። ቀደም ሲል አገልግሎቱ ባለመኖሩ ዳያስፖራዎች በአገራቸው ልማት የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ግን እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲኖራቸው የንግድና ቱርዝም ተሳትፏቸው እንዲጠናከር እንዲሁም የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ዳያስፖራዎች በውጭ ምንዛሬ በሚከፍቱት የቁጠባ ሂሳብ የተሻለ የወለድ ክፍያ እንዲያገኙም ያስችላቸዋል። በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ የቤት፣ የመኪና እና ሌሎች ግዥዎችን እንዲያከናውኑ ብድር የሚያመቻችላቸው መሆኑንም አቶ ባጫ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዲያሰፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትም መንግሰት ለዲያስፖራው መብትና ጥቅም ሲል ያመቻቸውን አዲስ አሰራር አድንቀዋል። ዲያስፖራው ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሱንም ሆነ አገሩን ለመጥቀም እንዲሰራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።