ቀጥታ፡

ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የተሰጠው ትኩረት ኢኮኖሚውን እምርታ አንዲያሳይ አድርጓል

መቀሌ /ኢዜአ/ 23/01/2012 ዓ.ም አገራችን መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍና የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን መንግስት ባለፉት አመታት ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሰጠው ትኩረት እምርታ የተመዘገበበት መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትር ገለፀ፡፡ የፌደራልና የክልሎች የትራንስፖርት ሀላፊዎች በተጠናቀቀው ዓመት የስራ አፈጻጸምና በዘንድሮ እቅድ ላይ የሚመክሩበት የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት  የኢኮኖሚ እድገቱ ለማፋጠን የመሰረተ ልማት አውታር የሚኖረውን ሚና በመገንዘብ መንግስት ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ አፍስሷል፡፡ በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በሀገራዊ የባቡር ኔትወርክ ግንባታ፣ለአቬሽን ኢንዱስቱሪ እድገት  የኤርፖርቶችን ግንባታና መዳረሻዎችን ከማስፋፋት አንጻር እምርታ እንደተመዘገበ አለም የሚያውቀው ክንውን ነው ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ የአገሪቱን ግዙፍ ኢኮኖሚ በማሳለጥ ረገድና በህብረተሰቡ የእለተ ተእለት ኑሮ ዑደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ ” ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ቅድሚያ የአገራችን ሰላም በመጠበቅ ብዙ ሆነን እንደ አንድ አንድ ሆነን ደግሞ እንደብዙ መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡ በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች  እንደተሰሩ ሁሉ ያልተሻገርናቸው ችግሮች መኖራቸውንም ሚኒስቴር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሰራ ለመቀነስ የተደረገው ጥረት የሚጠበቀውን ያህል  ውጤት አለመመዝገቡንም አንስተዋል ። የሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑም የገጠሩ ማህበረሰብ ምርቱን ወደ ገበያ የሚያቀርብበት ሁኔታ ከማመቻቸት አንጻር ጉድለቶች እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡ የተዘረዘሩትን ጉድለቶች በማስተካከል የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል፡፡ በምክትል ርእስ መስተዳደር ማእርግ የትግራይ ክልል የንግድ ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብረሀም ተከስተ በበኩላቸው ባለፉት አመታት በተከናወኑ ከፍተኛ ስራዎች ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ የአፍሪካ አገሮች አንድዋ ሆናለች ብለዋል፡፡ ውጤቱ አገሪቱ የተከተለችው ልማታዊ ፖሊሲ፣የአመራር ብቃትና የህዝቦችዋን ጥረት ድምር ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ኢንቨስትመንት ከማስፋፋትና የኢኮኖሚ እድገት ከማሳለጥ አንፃር ሚናው የጎላ መሆኑንም ዶክተር አብረሃም ገልፀዋል ። የበለጸጉ አገራት ጋር ለመድረስ ብዙ ስራዎች ይጠበቅብናል ያሉት የቢሮ ሀላፊው ይህም በፖሊሲዎች ያለውን ክፍተት በማሻሻል የኢትዮጵያ ህዝብ የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መመለስ ይቻላል ብለዋል፡፡ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በሁለት ቀናት ቆይታቸው ባለፈው ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትና በዘንድሮ እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሔዳሉ ተብሏል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም