ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አቀፉን የአስትሮኖሚካል ኅብረት ሲምፖዚየም ታካሂዳለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አቀፉን የአስትሮኖሚካል ኅብረት ሲምፖዚየም ታካሂዳለች
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚካል ኅብረት ሲምፖዚየም ልታካሂድ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ። ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ኅብረት ሲምፖዚየምና የአፍሪካ አስትሮኖሚ ማኅበር የምክክር መድረክ ከመስከረም 26-30 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ይህን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ እንደተብራራው በሁለቱ መድረኮች ከ30 አገራት ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች፣ ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎችና ባለድርሻ ተቋማት ስለ አስትሮኖሚና ስፔስ ሳይንስ ይመክራሉ። በኢንስቲትዩቱ የአስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ ምርምር ክፍል ኃላፊ ዶክተር ማሪያና ፖቪች እንዳሉት በዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ኅብረት በተለያዩ አገራት በየዓመቱ የሚዘጋጁ ሲምፖዚየሞች አሉ። ኅብረቱ መቶኛ ዓመቱን እያከበረ ይህንንም ክብረ በዓል ያከናወናቸውን ስራዎችና ስኬቶች እየገመገመ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው። እስካሁን 355 ሲምፖዚየሞች የተካሄዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ሲምፖዚየሙን የምታካሂድ ሶስተኛዋ የአፍሪካ አገር ስትሆን በደቡብ አፍሪካና ቡርኪናፋሶ መሰል ሲምፖዚየም ተካሂዷል። ሲምፖዚየሙ በዘርፉ ልምድና እውቀት ያካበቱ ተመራማሪዎች ልምዳቸውን የሚያጋሩበትና ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ በሳይንስ ዘርፍ እየከወኗቸው ያሉ ተግባራትን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ የሚያስችል ነው ብለዋል። የምስራቅ አፍሪካ አስትሮኖሚ ለልማት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ አለምዬ ማሞ በበኩላቸው እንደገለጹት የአፍሪካ አስትሮኖሚ ማኅበር የሚያዘጋጀው የአፍሪካ አስትሮኖሚ የሳይንስ ምክክር መድረክ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። መድረኩ በአፍሪካ አስትሮኖሚ ምን አይነት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል የሚያመላክት ራዕይና ስትራቴጂ ሰነድ የሚነደፍበት ይሆናል ነው ያሉት። የማኅበሩን እንቅስቃሴ ለሳይንስና ለጠቅላላ ማኅበረሰቡ ማስተዋወቅ፣ የአህጉሪቱ ወጣት ተመራማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማስቻል፣ በአፍሪካ በአስትሮኖሚና ስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የሚሰሩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማጎልበት የመድረኩ ዓላማዎች መሆናቸውን አንስተዋል። መድረኩ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርና ትስስር መፍጠር ያስችላልም ነው ያሉት። ነገና ከነገ በስቲያ አራት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ በዘርፉ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ላሉ ተማሪዎች የእውቀትና ክህሎት ስልጠናም ይሰጣል። ከሁለቱ መድረኮች ጎን ለጎን በተመረጡ 10 የህዝብ ትምህርት ቤቶች በተግባር የታገዘ አስትሮኖሚን የማስገንዘብ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል። ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስለ አስትሮኖሚ ሳይንስ ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም ለሁለተኛ ደረጃ መምህራን የሚሰጥ ስልጠና መኖሩም ተጠቁሟል።