ቀጥታ፡

ፕሮፌሰሩ በውጭ አገራት የሚሰሩ ሳይንቲስቶች ወጣቶችን በሳይንስ በማነጽ ተግባር እንዲሰማሩ ጠየቁ

አዲስ አበባ መስከረም 23/2012 ዕውቁና አንጋፋው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ ጥላሁን ይልማ በውጭ አገራት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች ወጣቶችን በሳይንስ በማነጽ ተግባር እንዲሰማሩ፤ መንግስትም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቀረቡ። ፕሮፌሰር ጥላሁን በቻይና ከሚገኙ የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ የአፍሪካ ሞሌኪዩራል ባዮሎጂ ላብራቶሪ ማዕከል ሊያቋቁሙ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ዕውቁ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሚዘጋጀው ወርኃዊ የሳይንስ ገለጻ መድረክ 'ወጣቱን ትውልድ ማስተማርና ማነጽ ለኢትዮጵያ ተስፋ፤ የቻይና ተምሳሌትነት' በሚል ትናንት ምሽት ገለጻ አድርገዋል። በአውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1943 በኢትዮጵያ የተወለዱት ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ ጥላሁን ይልማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ የግብርና ቴክኒካል ትምህርት ቤቶች አጠናቀው በቀድሞው የአለማያ እርሻ ኮሌጅ ለሁለት ዓመት ተከታትለዋል። ከዛሬ 55 ዓመታት በፊት በኮሌጅ ቆይታቸው ባሳዩት የላቀ ውጤትም አሜሪካን አገር በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ትምህር ቤት ተልከው ትምህርታቸውን በማጥናት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በቢሾፍቱ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት አስተምረዋል። ከሁለት ዓመታት በኋላም ወደ ካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ የ3ኛ ዲግሪያቸውን በደቂቀ ሥነ ሕይወት መስክ በማጥናት በአውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1980-2006 በተማሩበት ካሊፎርኒያ በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከረዳት እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አስተምረዋል፤ ተመራምረዋል። እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ ደግሞ የ'ዲስቲንጉሽድ ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ' ማዕረግ ያገኙ ሲሆን እ.አ.አ ከ1990 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፍ የሃሩራማ አካባቢ በሽታዎች የሞሌኪዩራል ባዮሎጂ ላብራቶሪ ማዕከል በማቋቋም በዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ። የፕሮፌሰር ጥላሁን ምርምሮች በቫይረስ ጥቃት በእንስሳትና በሰው ላይ ለሚከሰቱ በሽታዎች በዘረመል ምህንድስና ጥበብ ክትባት ወይም መከላከያ መድሃኒት ግኝቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። በዚህም የበርካታ በሽታዎች ክትባትና መድሃኒት ግኝቶች ባለቤት ሲሆኑ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር ያደረጋቸው 'ደስታ' በተሰኘውና ከ100 ዓመት በፊት በአውሮጳና በአፍሪካ ከፍተኛ ዕልቂት ላደረሰው የከብቶች መቅሰፍት በሽታ ክትባት መፈልሰፋቸው ነው። ይህን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በርካታ የምርምር ተቋማት ደክመው ያላሳኩትን የደስታ በሽታ ክትባት ማግኘታቸው በህክምና ግኝቶች መስፈርት አንቱ አስብሏቸዋል፤ ዓለምንም በደስታ በሽታ ከሚደርሰው እልቂት ታድገዋል። በእንግሊዝና በጣሊያን ወታደሮች ሴራ ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ከብቶች በተዛመተው የደስታ በሽታ እ.አ.አ ከ1888-1892 ለአራት ዓመታት በኢትዮጵያ በደረሰው እልቂት ከፍተኛ ረሀብ መከሰቱን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ጥላሁን የምርምራቸው መነሻ ከወላጆቻቸው ስለ ከብት መቅሰፍት ሲሰሙ ማደጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። በሰውና በእንስሳት ህክምና ዕውቀት በሁለቱም ሰይፍ የተካኑት አንጋፋው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን፤ ለኤች አይ ቪ/ኤዲስ ቫይረስ ክትባት ለማግኘትም ደክመዋል። ከ124 በላይ የሚሆኑ የምርምር ግኝቶች በስመ ጥር ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች የታተሙላቸው ሲሆን በአሜሪካና በቻይና በሚገኙ በርካታ ተቋማትም የአካዳሚ አባልነት ተመርጠዋል፤ በአማካሪነትም እየሰሩ ይገኛል። በተማሩበት ብሎም ባስተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ በአሜሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ዕውቅናና ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ለአብነትም የዩኒቨርሲቲዎች የምርጥ አስተማሪነትና ተመራማሪነት ሽልማት፣ የእንስሳት ህክምና ዘርፍ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ ሽልማት፣ የልዩ አገልግሎት ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። እርሳቸው ባቋቋሙትና በዳይሬክተርነት በሚመሩት የዓለም አቀፉ የሃሩራማ አካባቢ በሽታዎች የምርምር ማዕከል ከተለያዩ ታዳጊ አገራት በርካታ ሳይንቲስቶችንም አፍርተዋል። በትምህርትና ምርምር ዘመናቸው የነጮችን የዘረኝነት ጫና በመቋቋም ከስኬት ማማ ላይ የደረሱት ፕሮፌሰር ጥላሁን፤ አሁን ላይ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ወጣት ሳይንቲስቶችን በማስተማርና በማበረታት ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት ላይ ይገኛሉ። በወቅቱ ፖለቲካ ምክንያት መገለል ደርሶባቸው ከ26 ዓመታት በኋላ እናት አገራቸውን የረገጡት ፕሮፌሰሩ፣ አሁን በተገኘው አገራዊ ተስፋ ወደ አገራቸው ተመልሰው በሙያቸው አበርክቶ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። በዚህም ቢ.ጂ.አይ. ከተሰኘው የቻይና የሳይንስ ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር በካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋሙት አይነት የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ ለማቋቋም ጥረት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያዊ ማንነትና ታሪካቸው አብዝተው የሚኮሩትና ከፊታውራሪ ጎራው ገበየሁ ቤተሰብ መወለዳቸውን የሚናገሩት ሳይንቲስቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካና ስርዓተ ትምህርት መበላሸት አንዱ መንስኤ የምዕራባዊያን ተንኮል መሆኑን ገልጸዋል። 'ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ነገር የመፍጠር አዕምሮ ባለቤቶች ነን፤ ሰርተንም አሳይተናል' ያሉት ፕሮፌሰር ጥላሁን በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ወጣቱን ትውልድ በሳይንስ በማነጽና በማስተማር ስራ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል። ሳይንቲስቱ በተለይም ለኢዜአ እንደተናገሩት በምዕራባዊያን ሴራ ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባትገባ ኖሮ እንደ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን የመሆን ዕድል ይኖራት ነበር ይላሉ። የምሁራን ኩብለላን በመታደግ በውጭ የተማሩና የሚሰሩ ሳይንቲስቶችን በመጠቀም ከቻይና መማር እንደሚገባም ገልጸዋል። ወጣቱን ለማነጽ ለሚሰሩ ስራዎችም መንግስት ሳይቲስቶችን ማገዝ እንዳለበት ተናግረዋል። አንጋፋ ተመራማሪዎች ወጣቱን ማስተማር እንዳለባቸው ገልጸው፤ እርሳቸውም በሚዲያም ሆነ በሌሎች መድረኮች ወጣቱን ስለ አንድነትና ስለ ስራ የማስተማር ተግባራት ላይ እንደሚያተኩሩም ገልጸዋል። በሌላ በኩል በሳይንስ መስክ ለማከናወን የወጠኑት ስራ ዕውን እንዲሆን ተባባሪ አባል የሆኑበትን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን በመጠቀም እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 'አንድ አገር፣ ተከባብሮና ተዋዶ የሚኖር አንድ ህዝብ፣ አንድ ባንዲራ፣ አንድ የሳባ ፊደል ይዘን እንራመድ'ሲሉ ሳግ እየተናነቃቸው ንግግራቸውን የቋጩት ፕሮፌሰር ጥላሁን የሳይንስ ባህል ያለው ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። በሰፊው አዳራሽ ሰፊ የሳይንስ ዕውቀት ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት በታደሙበት መድረክ ለፕሮፌሰር ጥላሁን ከተሳታፊዎች ዘንድ የላቀ ከበሬታና ምስጋና ቀርቦላቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም