የኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የውጭ ማምረቻ ዘርፉን እየሳበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የውጭ ማምረቻ ዘርፉን እየሳበ ነው
መስከረም 23/201 በቻይናና በእስያ አገራት እየጨመረ የመጣው የማምረቻና የጉልበት ዋጋ አምራቾች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲያማትሩ አስገድዷቸዋል ተባለ። ይህ ለአፍሪካ ከፍ ያለ ዕድል ይዞ እንደመጣ የጠቀሰው ሀው ሜድ ኢን አፍሪካ የተሰኘ ድረ-ገጽ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ተመራጭ በመሆን በዕድሉ እየተጠቀመችበት ነው ብሏል። ኢትዮጵያ አሁን ላይ ዝቅተኛ የተባሉ ነገር ግን የስራ ዕድልን በስፋት የሚፈጥሩ የማምረቻ ፋብሪካዎችን በገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት በመሳብ ላይ ትገኛለች። ድረ-ገፁ እንዳለው እ.አ.አ 2018 ብቻ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ኢንቨስትመንቶችን ወደ አገር ውስጥ መሳብ ችላለች። የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶችና ጫማዎች የሚያመርቱት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትኩረት የተቸራቸው ናቸው። የመሰረተ ልማት ግንባታውን በማስፋፋትና በማሻሻል እንዲሁም ኢኮኖሚውን ነፃ በማድረግ በአፍሪካ ሰፊ ካፒታል የሚጠይቁ አምራቾችን ትኩረት መሳቧም ተነግሯል። እነዚህ ፋብሪካዎች የወጪ ንግዱን የሚያሳድጉና የአፍሪካን ሸማቾች የኢኮኖሚ አቅርቦት ማሻሻል የሚችሉ ናቸው። በተመሳሳይ ራንድ መርቸንት ባንክ በአፍሪካ የት ኢንቨስት ማድረግ ትችላላችሁ? ሲል ባወጣው ወቅታዊ ሪፖርት የአገራቱን የኢኮኖሚ እምቅ አቅምና የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተከትሎ ምልከታውን አስቀምጧል። ተቋሙ ባወጣው ደረጃ ኢትዮጵያን ዘጠነኛ ላይ ያስቀመጣት ሲሆን "ከፍ ያለ ተፈላጊነት ያላት አገር" በማለት ጠቅሷታል። ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሆነችና ለሸቀጦችና አገልግሎቶች ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ገልጿል። ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበሩት ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስትመንቱን ወደኋላ እንደጎተቱት በመጥቀስ አሁን ላይ ሂደቱ በመለወጥ ላይ መሆኑን አስታውቋል። መንግስት ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ እየወሰደ ያለው ስር ነቀል ለውጥ በቁጥጥሩ ስር የነበሩትን የቴሌኮምና የኃይል ማመንጫ ዘርፎች በከፊል ለባለሃብቶች ክፍት ወደ ማድረግ አሳድጎታል። በአገሪቱ ንግድ ለማከናወን ያለው ውጣ ውረድ ኢትዮጵያን ከተቀመጠችበት ደረጃ ከፍ እንዳትል እንዳደረጋትም ተመልክቷል። ኢትዮጵያም ይህን መሰናክል ለማስቀረት የአንድ መስኮት አገልግሎት በመክፈት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት በመከወን ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል። የቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩና በዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት የነበሩት ጀስቲን ሊን እ.አ.አ 2012 ባሰፈሩት ፅሁፍ ቻይና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ጉልበት ተኮር የሆኑ 85 ሚሊዮን የማምረቻ ዘርፍ የስራ ዕድሎችን ታጣለች ብለው ነበር። በተመሳሳይ መንገድ ጃፓን በ1960ዎቹ አስር ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን ስታጣ ኮሪያም በ1980ዎቹ የጉልበትና የማምረቻ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን አጥታለች። አሁን ላይ የቻይና ኢኮኖሚ በተመሳሳይ መንገድ መጓዙን ተከትሎ ኢትዮጵያና ብዛት ያላቸው የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ በዕድሉ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።