ቀጥታ፡

የኢህአዴግ ውህደት በፌዴራሊዝሙ ስርዓት ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ የለውም - የአጋር ድርጅቶች አመራሮች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) መስከረም 23 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊፈጥረው ያሰበው አንድ ውህድ ፓርቲ በኢትዮጵያ ተግባራዊ በሆነው የፌዴራሊዝም ስርዓት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽእኖ እንደማይኖረው ኢዜአ ያነጋጋራቸው የአጋር ድርጅት ሊቃነ መናብርት አስታወቁ። ውህደቱ አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ድምጽ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ሊቃነ-መናብርቱ ጨምረው ገልጸዋል። ኢህአዴግ  "ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) " በተባሉ አራት እህት ድርጅቶች የተፈጠረ ግንባር  ነው። ግንባሩ  የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ቤጉህዴፓ)፣ የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን)፣ የሶማሌ ህዝቦች ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ) እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) የተባሉ አምስት ፓርቲዎችን ደግሞ በአጋርነት ይዟል። የግንባሩ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ ከአንድ ዓመት በፊት በሐዋሳ ከተማ  በተደረገው የኢህአዴግ 11ኛው ጉባኤ  ላይ ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ  ማምጣት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን በይፋ መናገራቸው ይታወሳል። ጉባኤው የአጋር ድርጅት ሊቃነ መናብርትና  ምክትሎቻቸው በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ያለ ድምጽ ተሳትፎ እንዲያደረጉ ያስቀመጠው ውሳኔም ገቢራዊ እየተደረገ ይገኛል። ኢዜአ የኢህአዴግን ውህደት አስመልክቶ የሐብሊ፣ ቤጉህዴፓና የጋህዴን ሊቃነ መናብርትን አነጋግሯል። የሐብሊ ሊቀ መንበር አቶ ኦርዲን በድሪ አጋር ድርጅቶች የኢህአዴግ አባል ለመሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበር አስታውሰዋል። ''ነገር ግን ለጥያቄያችን ውሃ የማይቋጥሩ የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ እስካሁን ቆይተናል'' ብለዋል። አጋር ድርጅቶች በመሆናቸው ብቻ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው መደረጉን በማብራራት፤ ''እኛ ያልተሳተፍንበትና በእህት ድርጅቶች የተቀመጡ ውሳኔዎችን ደግሞ ገቢራዊ እናደርጋለን'' ብለዋል። ውህደቱ  አጋር ድርጅቶች በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ እድል በመፍጠር በውሳኔ ሂደት ተሳትፎ ሳያደርጉ ተግባራዊ የሚያደርጓቸውን ጉዳዮች ለማስቀረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። አንዳንድ አካላት ውህደቱን 'በጨፍላቂነት' በመፈረጅ የአገሪቱን የፌዴራሊዝም ስርዓት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ሲናገሩ መስማታቸውን ገልጸው፤ ''ውህደቱ የፓርቲ ጉዳይ እንጂ  አገሪቱ እየተመራችበት ካለው ህገ መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም'' ብለዋል። ህገ መንግስቱ በስራ ላይ እስካለ ድረስ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ  ባለበት እንደሚቀጥልም አቶ ኦርዲን ጨምረው ገልጸዋል። የጋህዴን ሊቀመንበር አቶ ኡመድ ኡጁሉ በበኩላቸው ውህደቱ ለአጋር ድርጅቶች የውሳኔ ሰጭነትን እድል እንደሚያጎናጽፋቸው ተናግረው፤ "ይህም ለፌዴራሊዝም ስርዓቱ መጠናከር ሚናው የጎላ ነው" ብለዋል። በአንድ ፓርቲ ስር የሚዋሃዱት ሁሉም አካላት እኩል የመደራረደር አቅም እንደሚኖራቸው በመግለጽ። የቤጉህዴፓ ሊቀመንበር አቶ አሻድሌ ሃሰን ''በፌደራሊዝም ስርዓት የተዋቀረች  ኢትዮጵያን እኩል እያስተዳደርን አጋር ድርጅት በሚል ምክንያት ብቻ በውሳኔ ሰጭነት አለመሳተፋችን ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ፈጥሮብናል'' በማለት ውህደቱ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። ውህደቱ  ሁሉም አካላት በአንድ ጠረጴዛ  እኩል እንዲመክሩና እንዲወስኑ  እድል በመፍጠር ልጆቿን በእኩል የምታይ ህብረ ብሄራዊ አገር የመፍጠሩ  ሂደት ላይ  አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል። ነገር ግን እህትና አጋር የሚለው አሰላላፍ ለግል ጥቅማቸው የሚመቻቻው አካላት ውህደቱን ጥላሸት የመቀባት ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚችሉም አቶ አሻድሌ  ተናግረዋል። ስለውህደቱ ግልጽና ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር በሂደቱ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን መከላከል እንደሚገባም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም