ቀጥታ፡

የሚፈለገውን ደም ከሕብረተሰቡ ለመሰብሰብ እንዳልቻለ የሁመራ የደም ባንክ ማዕከል አስታወቀ

ሁመራ (ኢዜአ) መስከረም 22 ቀን 2012 የሁመራ ደም ባንክ ማዕከል ከህብረተሰቡ ለማግኘት ያቀደውን ደም ለመሰብሰብ መቸገሩን ገለጸ። የሁመራ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው የደም ልገሳ ፋይዳን አስመልክቶ ተከታታይ የግንዛቤ ትምህርት ለህብረተሰቡ መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል። ማዕከሉ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ለመሰብሰብ ካቀደው የደም መጠን ግማሽ ያህል ብቻ መሰብሰቡ ተመልክቷል። የሁመራ ደም ባንክ ማዕከል አስተባባሪ አቶ እምነቱ ገብረእግዚብሔር ለኢዜአ እንዳሉት በ2011 በጀት ዓመት 3 ሺህ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ ቢታቀድም ማሳካት የተቻለው 1 ሺህ 661 ከረጢት ደም ብቻ ነው። በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ባሉ አራት ወረዳዎች ከህብረተሰቡ ደም ለመሰብሰብ ማዕከሉ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ደም መሰብሰብ አልተቻለም። ማዕከሉ ያለበት የተሽከርካሪና የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም የሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ደም በሚፈለገው ልክ እንዳይሰበሰብ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል። "ከእዚህ በተጨማሪ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላትና አመራሮች ትብብር ማነስ ለዕቅዱ አለመሳካት አስተዋጽኦ አድርጓል"  አቶ እምነቱ። እንደአስተባባሪው ገለጻ የደም ባንክ ማዕከሉ በ2012 በጀት ዓመት ከ2ሺህ 300 በላይ የደም ከረጢት ለመሰብሰብ አቅዶ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ለዕቅዱ መሳካት ሕብረተሰቡ ደም በመለገስ የበኩሉን ሚና እንዲጫወትም አቶ እምነቱ ጥሪ አቅርበዋል። የሁመራ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሙሉብርሃን ነጋሽ በበኩሉ ከግንዛቤ እጥረት ማነስና ከፍርሀት የተነሳ እስካሁን ድረስ ደም ለግሶ እንደማያውቅ ተናግሯል። " ደም ብለግስ የጤና እክል ያጋጥመኛል የሚል ስጋት አለብኝ " ሲልም ተናግሯል። "ደም መለገስ ሌሎችን የማትረፍ ዓላማ እንዳለው ባውቅም ሌሎች ብዙ ሰዎች የግንዛቤ ትምህርት ስለሌላቸው ደም ለመለገስ ሲነሳሱ እይታይም ‘‘ያለችው ደግሞ የሁመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ሃይማኖት ዳኘው ናት። "በቀጣይም ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ካልተሰጠ የሚፈለገውን ደም ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ይሆናል" ስትልም ስጋቷን ገልጻለች። ፋንታሁን ዜናዊ የተባለ ወጣት በበኩሉ ከእዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ደም መለገሱንና በእዚህም ምንም አይነት የጤና እክል እንዳላጋጠመው ተናግሯዋል። ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉ እንዲዳብር የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን የገለጸው ወጣቱ፣ በመንግስት በኩል ህብረተሰቡን የማሳወቅ ስራ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል። በመሆኑም የአከባቢው ህብረተሰቡ ደም በመለገስ አጋዥ ሚናውን እንዲጫወት ነው ጥሪው ያስተላለፈው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም