የሁሉም ብሔሮች ባህል እንደ ድርና ሸማ በአንድነት ሲሸመን የኢትዮጵያ ባህል ይሆናሉ - ዶክተር ሂሩት ካሳው - ኢዜአ አማርኛ
የሁሉም ብሔሮች ባህል እንደ ድርና ሸማ በአንድነት ሲሸመን የኢትዮጵያ ባህል ይሆናሉ - ዶክተር ሂሩት ካሳው
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 22 2012 የሁሉም ብሔሮች ባህል እንደ ድርና ሸማ በአንድነት ሲሸመን የኢትዮጵያ ባህል ይሆናሉ ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ። የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አስመልክቶ 'የኢሬቻ የሰላምና የአንድነት ፎረም' በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በፎረሙ የታደሙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ''በክፉም ሆነ በበጎ ጸንተን አብረን እንድንኖርና ጠላቶቻችንን እንድንመክት ያደረጉን አባቶቻችን ያቆዩልን ባህሎቻችን ናቸው'' ብለዋል። ''ኢትዮጵያ የባህል ባለጸጋ ነች'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያ ባህል የሚባለውም የእያንዳንዱ ብሔር ባህል የድምር ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል። ''እያንዳንዱ ብሔር የየራሱን ከጠበቀ፣ ለሌላው ካካፈለ እና ካሳደገ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ዘመን ይሻገራል'' ብለዋል። ''በቀደምት ወገኖቻችን እንደምንኮራ ሁሉ የእነሱ አንጡራ ሀብት በሆነው ባህላዊ እሴቶቻችን ልንኮራ ይገባል'' ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ ከእነዚህ ድንቅ በዓላት መካከል ኢሬቻ አንዱ የፍቅር መገለጫ በዓል መሆኑን አውስተዋል። እንደ ኢሬቻ ያሉ በዓሎችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥልቅ ምርምር ተደርጎባቸው በትምህርት ስርአት ውስጥ እንዲካተቱ ምሁራን ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሁሉም የማንነት መገለጫ የሆነው ኢሬቻ ይበልጥ እንዲደምቅ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። ''የአንድነት፣ የፍቅርና የሰላም በዓል የሆነው ኢሬቻ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በዓልነት አልፎ በአፍሪካም ደረጃ እንዲከበርም መስራት ይገባል'' ብለዋል። የፎረሙ ዓላማም ምሁራን ይበልጥ አጥንተው ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን መፍቻ እና ለአገር ፖሊሲ ግብዓት እንዲሆን ማስቻል መሆኑን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል። በቀጣይ የሚከበረውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ከመላ አገሪቱ እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ እንግዶች በአክብሮትና በሰለጠነ ሁኔታ በሰላም ህዝቡ ሊያስተናግዳቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ሃይሉ በዓሉን መሰረት አድርጎ የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። በፎረሙ የጥናት ሃሳባቸውን ያቀረቡት አቶ ስንታየሁ ቶላ ኢሬቻ የገዳ ስርዓት ውስጥ ከሚንጸባረቁት ሁነቶች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል። ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ረዳት ፕሮፈሰር አሰቦ ረጋሳ በበኩላቸው ኢሬቻ ለሰላምና ለአገር ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ኢኮኖሚ ማህበር የመጡት ዶክተር ጉቱ ቴሶ ኢሬቻ በአቃፊነቱ፣ በይቅር ባይነቱ፣ በአንድነቱ፣ በተለይም ንግድና ቱሪዝምን በማሳለጥ ለአገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።