የአዋላጅ ነርሶች የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እያገዙ እንደሆነ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዋላጅ ነርሶች የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እያገዙ እንደሆነ ተገለጸ
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 22 2012 የአዋላጅ ነርሶች የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እያገዙ እንደሆነ የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ገለጸ። የኢትዮጵያ የአዋላጅ ነርሶች ማህበር 28ኛ አመታዊ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዘነበ አካለ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የአዋላጅ ነርሶችን በቁጥርና በጥራት ማሳደግ መቻሉ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን እያገዘ መሆኑን ገልጸው ፤ በየክልሉ ያሉት የአዋላጅ ነርሶች ቁጥር ማነስ እናቶች በቅድመ ወሊድ ሆነ ከወሊድ በኋላ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዳያገኙ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። የሙያ ማህበሩ ዓላማ የእናቶችን ሞትና ህመም መቀነስ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ዘነበ፤ ዓላማውን ለማሳካት የሚያስችል የሙያተኛ ቁጥርና ጥራት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ''በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅቶች አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ የእናቶችን ሞት መቀነስ እንችላለን'' ብለዋል። ''ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ሙያው ማደግ ይጠበቅበታል'' ያሉት ዶክተር ዘነበ፤ የሙያ ማህበሩ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ሁሉም እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ በስፋት መሰራት እንዳለበት ያስገነዘቡት የሙያ ማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በቤት መውለድ ለደም መፍሰስ እና ለተራዘመ ምጥ የሚያጋልጥ በመሆኑ አደጋ እንዳለው ገልጸዋል። የደም መፍሰስ አደጋ ለሞት እንደሚያበቃና የተራዘመ ምጥ ፌስቱላን ለመሳሰሉ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ተናግረዋል። በየአመቱ ከ3 ሺህ 500 በላይ አዳዲስ የፌስቱላ ህሙማን እንደሚከሰትም ፕሬዘዳንቱ አመልክተዋል። በ1984 ዓ.ም የተቋቋመው የአዋላጅ ነርሶች ማህበር ከ5 ሺህ 500 በላይ አባላት አሉት።