በትግራይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ለመቀነስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ለመቀነስ እየተሰራ ነው
መስከረም 22/2012 በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ፅህፈት ቤት አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት አሁን የሚታየውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ ። ፅህፈት ቤቱ ያለፈው አመት የስራ አፈጻጸምና በያዝነው አመት ሊፈታቸው ያቀዳቸውን የህብረተሰብ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል። ከስምንት ዓመታት በፊት መብራት እንዲያገኙ ክፍያ ፈጽመው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ከ6 ሺህ በላይ ደንበኞችም ዘንድሮ ምላሽ ያገኛሉ ብሏል ። የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን በመግለጫው እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት በክልሉ የነበረውን ከፍተኛ የሃይል መቆራረጥ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ስለሚያጋጥም በህብረተሰቡን ዘንድ ቅሬታ አስከትሎ ነበር ብለዋል ። ለህብረተሰቡ ለመብራትና ምግብ ማብሰያና ለፋብሪካዎች አገልግሎት የሚውል የኤሌክትሪክ መስመር አንድ ላይ በመዘርጋቱ ችግሮቹ እንዳባባሳቸው በጥናት መለየቱንም አቶ መስፍን ገልፀዋል። ችግሩ ለመቅረፍም የሰው ሃይል፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስሪያ እቃዎች ፣ የመብረቅ መከላከያና ለስራ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች የግብአት አቅርቦት ለማሟላት ጥረት ተደርጓል ። በኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች የስነምግባር ጉድለት ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ የተነሱ ቅሬታዎች ለመፍታትም ለሰራተኞቹ የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠቱን ተናግረዋል። ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ሰራተኞች ከተገኙም እርምጃ ለመውሰድ የሚያስገድድ ስርአት ተዘርግቷል ብለዋል ። በአክሱምና በሽረ እንዳስላሴ ከተሞች የተጀመረው የፋብሪካዎችንና የህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመሮች የማለያየት ስራም በሁሉም የክልሉ ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል ። ከ2004 ዓም ጀምረው የመብራት አገልግሎት ለማግኘት ክፍያ የፈጸሙ 6 ሺህ 500 ደንበኞች በዚህ አመት ሙሉ በሙሉ ጥያቅያቸው ለመመለስ ጥረት እንደሚደረግም ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል ። ለ40 ሺህ ደንበኞች የሚሆን እቃ በእጃችን ይገኛል ያሉት አቶ መስፍን በዚህ አመት በተለይ የቆጣሪ ችግር ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፍ ነው የተናገሩት። ፅህፈት ቤቱ ባለፈው አመት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽያጭ ከ573 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ገልጸዋል። በዚህ በጀት አመትም 825 ሚሊዮን ብር ከደንበኞቹ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ነው ያሉት አቶ መስፍን ገቢው በዚህ አመት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኛሉ ተብሎ የታቀቀደው 77 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል። በትግራይ ክልል ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የተያያዙ የህብረተሰቡ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ኢዜአ በተደጋጋሚ መስራቱ ይታወሳል።