ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ ኤሲሲ የአቪዬሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋራ ያለውን ትብብር ማስፋቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ኢዜአ/ መስከረም 22/2012 ዓለም አቀፉ የኤርፖርት አማካሪዎች ምክር ቤት (ኤሲሲ) የአቪዬሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋራ ያለውን ትብብር ማስፋቱን አስታወቀ። ዋና መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው የኤሲሲ አቪዬሽ ኩባንያ የአውሮፕላን ኪራይን፣ የአየር ትራንሰፖርት ሥራ አመራርን እና ማማከርን ጨምሮ በተለያዩ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፎች አገልግሎቱ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። ኩባንያው በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር ለመስራት የሚያስችል ውል መፈረሙ የሚታወስ ነው። በዚህ ውል መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓ የሚያከናውናቸውን ከበረራ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ተግባራትን ኩባንያው በወኪልነት ያስፈፅማል። አየር መንገዱ የገባው ውል በአውሮፓ ውስጥ ያለውን ገበያ ለማጠናከር ሰፊ እድል እንደሚፈጥርለትም ከዚህ በፊት ገልጾ ነበር። አሁን በተደረሰው ስምምነት መሰረት ደግሞ ኤሲሲ የአቪዬሽን ኩባንያ ከአውሮፓ በተጨማሪ አየር መንገዱ በሰሜን አሜሪካና እስያ ከበረራ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በወኪልነት የሚያስፈጽም መሆኑን ኩባንያውና አየር መንገዱ ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል። ከዚህ በፊት ከነበሩት ከተሞች ውጭ በአሜሪካ ሂውስተን፣ በቻይና ሻንጋይና ቼንግዱ፣ በእንግሊዝ ማንችስተር፣ በጣልያን ሮም እና በሩሲያ ሞስኮ ከተሞች በኤርባስ 350፣ በቦይንግ 787-8 እና 787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች አየር መንገዱ የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎት ኩባንያው ወኪል ሆኖ እንደሚያስተዳደርም በመግለጫው ተመልክቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የስትራቴጂክ እቅድ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቡሴራ አወል አየር መንገዱ ከኤሲሲ አቪዬሽን ኩባንያ ጋር ያለው ትብብር ከአውሮፓ አልፎ በሌሎች አህጉራት አየር መንገዱ ያለውን አገልግሎት እንዲያሰፋ አድርጎታል ብለዋል። በተጨማሪ አየር መንገዱ በደንበኞች አገልግሎት እንዲሁም በበረራ አገልግሎት ተአማኒነት እና ደህንነት ያለው ጠንካራ አቅም ለማሳየት እንዳገዘውም ተናግረዋል። አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን እያሰፋ ያለው አየር መንገዱ ከኤሲሲ ጋር በትብብር መስራቱ የሚታወቅበትን የአገልግሎት ጥራት የበለጠ እንዲያስተዋውቅ እንደሚረዳውም ነው አቶ ቡሴራ የገለጹት። የኤሲሲ የአቪዬሽን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ፒል ማቲውስ በበኩላቸው ኩባንያቸውና አየር መንገዱ ያላቸው የስራ ግንኙነት ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገና እየጠነከረ መጥቷል ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም