ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ወጥ የምርምር ስርአት ለመዘርጋት ብሄራዊ የሳይንስና ምርምር ካውንስል ማቋቋም ያስፈልጋል ተባለ

መስከረም 22/2012 በአገሪቷ ወጥ የምርምር ስርአት ለመዘርጋት ብሄራዊ የሳይንስና ምርምር ካውንስል ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አስታወቀ። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ የሳይንስና ምርምር አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በአውደ ጥናቱ ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ፣ ከምርምር ተቋማትና ከሞያ ማህበራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ ማርያም እንደተናገሩት በአገሪቷ በሳይንስ ዘርፉ ብቃትና አቅም ያላቸው ተማራማሪዎች ቢኖሩም ምርምሮች ወጥ ባልሆነና ቅንጅት በጎደለው መልኩ እየተከናወኑ ይገኛል። በመሆኑም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወንና ምርምሮች ላይ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ብሄራዊ የሳይንስና ምርምር ካውንስል ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል። የካውንስሉ መቋቋም በአገሪቷ ወጥ የሆነ የምርምር አሰራር ስርአት ለመዘርጋት፣ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል፣ በጀትና የምርምር መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቁመዋል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር የሳይንስና የምርምር ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በበኩላቸው ካውንስል ቢቋቋም የሳይንስ ዘርፍ ለአገሪቷ ዕድገትና ልማት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በሳይንስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት ተሞክሮም የካውንስሉን መቋቋም ጠቀሜታ ያረጋግጣል ብለዋል። የሚንስቴሩን አደረጃጀት የመፈተሽና በተገቢው መልኩ የማዋቀር ምርምሮችን ለመከታተል የሚያስችል የመረጃ ስርዓት የመዘርጋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል። በአገር ወስጥ የሚታተሙ የምርምር ጆርናሎችን ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል። የዩንቨርስቲ ኢንደሰትሪ ትስስር ያለመጎልበት፣ የምርምር ተቋማት ቅንጅት ክፍተት፣ በሳይንስ ፖሊሲና አገራዊ ልማት አጀንዳ ላይ የምሁራን ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን በዘርፉ ከሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸውንም ዶክተር ሰለሞን አብራርተዋለ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉትም የሳይንስና ምርምር አውደ ጥናቱ ዋነኛ ትኩረት በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ምርምሮች ጥራት፣ በጀት፣ ስርጭትና ውጤቶችን ለመዳሰስ ነው። በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን መለየትና በተለያዩ ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮች ተግባራዊነትን መዳሰስም የአውደ ጥናቱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል። ከአውደ ጥናቱ በሳይንስ ዘርፉ ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው ዘርፉን ለማሳደግ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም