ቀጥታ፡

መንግስት የሚያስተዳድራቸው 12 የልማት ድርጅቶች በተያዘው ዓመት ወደግል ይዛወራሉ

መስከረም 22/2012 መንግስት የሚያስተዳድራቸውን 12 የልማት ድርጅቶች በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ ወደግል ለማዘዋወር እንቅስቃሴ መጀመሩን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ዛሬ በሰጠው መግለጫ ያለፈውን በጀት ዓመትና የቀጣዩን ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ  አስመለክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክር አቶ በየነ ገብረ መስቀል እንደገለጹት፣ በመንግስት ይዞታ ስር ካሉት የልማት ድርጅቶች መካከል በተያዘው በጀት ዓመት 12ቱን  ወደ ግል ለማዞር በጥናት የተደገፈ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉ ወደግል ለማዘዋወር የሚያስፈልገው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል። ወደግል ከሚዘዋወሩት መካከል ስድስቱ የስኳር ፋብሪካዎች ሲሆን በስራቸውም 13 ፕሮጀክቶች እንዳሉ  አንስተዋል። ሌሎቹ የሂልተን አዲስ ሆቴል 70 በመቶ ድርሻ፣ የጊዮን ሆቴሎች ድርጅት፣ የላንጋኖ ሪዞርት፣ የፍል ውሃ አገልግሎትና ሶስት የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች መሆናቸውም ተመልክቷል። በሌላ በኩል ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ከልማት ድርጅቶች ምርትና አገልግሎት ሽያጭ 258 ቢሊየን ብር ማግኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በየነ አስታውቀዋል። በበጀት ዓመቱ ታቅዶ የነበረው የገቢ መጠን ግን 311 ቢሊየን ብር እንደነበር በማውሳት። እርሳቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 114 ቢሊየን ብር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 53 ነጥን 6 ቢሊየን ብር፣ ኢትዮ ቴሌኮም 36 ቢሊየን ብር እና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት 18 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በማስገባት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከልማት ድርጅቶች ከታክስ በፊት 52 ቢሊዮን ብር ትርፍ መገኘቱን ጠቅሰዋል። በበጀት ዓመቱ የታቀደው ትርፍ ወደ 70 ቢሊዮን ብር ይጠጋ እንደነበርም አመልክተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የኤጀንሲውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ከአዲሱ ተልእኮና ከዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ ጋር አጣጥሞ መቅረጽና መተግበር ከዋነኛ የኤጀንሲው የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል እንደሆነም ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮ-ቴሎኮምን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሚያስተዳድራቸውን ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደግል ለማዞር የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም