ቀጥታ፡

የብሔሮች ባህል ድምር ውጤት የሆነውን የኢትዮጵያ ባህል ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተለላፍ አለብን - ዶክተር ሂሩት ካሳው

መስከረም 22/2012 "የእያንዳንዱ ብሔር ባህል የድምር ውጤት የሆነው የኢትዮጵያ ባህል ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተለላፍ አለብን" ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ። የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አስመልክቶ 'የኢሬቻ የሰላምና የአንድነት ፎረም' በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በክፉም ሆነ በበጎም ጸንተን አብረን እንድኖርና ጠላቶቻችንን እንድንመክት ያደረጉን ባህሎቻችን ናቸው። "ኢትዮጵያ የባህል ባለጸጋ ነች፤ የእያንዳንዱ ብሔር ባህል የድምር ውጤት የሆነው የኢትዮጵያ ባህል ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን።" ብለዋል ሚኒስትሯ በንግግራቸው። እንደ ኢሬቻ ያሉ የፍቅር፣ የአንድነትና የአቃፊነት መገለጫ የሆኑ ባህሎች የህዝቡ በመሆናቸው መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥልቅ ምርምር ተደርጎባቸው በትምህርት ስርአት ውስጥ እንዲካተቱ ምሁራን ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሁሉም የማንነት መገለጫ የሆነው ኢሬቻ ይበልጥ እንዲደምቅ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። ''የአንድነት፣ የፍቅርና የሰላም በዓል የሆነው ኢሬቻ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በዓልነት አልፎ በአፍሪካም ደረጃ እንዲከበርም መስራት ይገባል'' ብለዋል። በዚህ ፎረም የሚቀርበው ጉዳይም ይበልጥ ዳብሮ በህትመት እንዲወጣ ተደርጎ ለህዝብ እንደሚቀር ነው አቶ ሽመልስ ገልጸዋል። ሰውን መሰረት አድርጎ ለእንስሳትና ለስነ ፍጥረታት በሙሉ የቆመውን የገዳ ስርአት ይበልጥ በማጥናትና በመመራመር ለአገር ፖሊሲና ስትራቴጂ ግብአት ለማድረግ መስራት እንደሚገባም ነው የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ያስረዱት። በቀጣይ የሚከበረውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ከመላ አገሪቱ እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ እንግዶች በአክብሮትና በሰለጠነ ሁኔታ በሰላም ህዝቡ ሊያስተናግዳቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ሃይሉ የኢሬቻ በዓል መሰረት አድርጎ የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። የፎረሙ አላማ የኢሬቻን በዓል አቃፊነትና የሰላም ተምሳሌትነት ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነም ተናግረዋል። የኢሬቻ የሰላምና የአንድነት ፎረም ከሰአትም ሲቀጥል በምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም