ቀጥታ፡

በአክሱም ዙሪያ የሚገኙ ጥንታዊ የብራና መጻህፍትና የወታደራዊ ዘውዶች ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ ትኩርት አልተሰጠም

አክሱም (ኢዜአ) መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም በአክሱም ዙሪያ የሚገኙ ጥንታዊ የብራና መጻህፍትና የወታደራዊ ዘውዶች ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ ትኩረት አልተሰጠም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። የገዳም አስተዳዳሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት ከአክሱም ከተማ ወጣ ብለው የሚገኙና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ በርከታ ቅርሶች ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ በትኩረት አልተሰራም። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የሚገኘው የአቡነ ጰንጠሊዎን ጥንታዊ ገዳም የሰበካ ወንጌል ኃላፊ ሊቀትጉሀን ካህሳይ ተስፋሚካኤል እንዳሉት ገዳሙ በርካታ ቅርሶች ቢኖሩትም ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች እንዲተዋወቅ አልተደረገም። በውስጡ የአጼ ካሌብ እና የአጼ ገብረመስቀል መቃብር እና በወቅቱ ይጠቀሙበት የነበረውን ወታደራዊ ዘውድ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል። ገዳሙ ከ1 ሺህ 500 በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ጥንታዊ የብራና መጻህፍትና መስቀሎችን የያዘ የቅርስ ስፍራ መሆኑን ሊቀ ተጉሃን ካሕሳይ አብራርተዋል። "ገዳሙ ብዙ ቅርሶች ይዞ ሳለ ትኩረት ተሰጥቶት በቱሪዝም ዘርፍ ሊለማና ሊተዋወቅ አልቻለም፤ በቀጣይ ጥቅም ላይ እንዲውል በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የሀጸቦወ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወጣት ታደስ ብርሀነ በበኩሉ ገዳሙ በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን ቢችልም እስካሁን ድረስ በሚገባ አለመተዋወቁን ነው የገለጸው። "የአክሱም ኃውልትን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ቢሆንም በአቅራቢያው የሚገኘውን የአቡነ ጴንጠሊዎን ገደም እንዲጎበኝ የሚደረግበት አሰራር አልተፈጠረም" ብሏል። "የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ገብኚዎች በስፍራው አይቼ አላቅም" ያለው ወጣቱ ከከተማዋ ወደ ገዳሙ የሚወስደውን መንገድ ለቱሪስቶች አመቺ የማድረግ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሟል። ገዳሙ በተራራ ላይ የተሰራ ስለሆነ ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ የመንገዱ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክቷል። በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የቅርስ አስተዳደር መምህር ዳንኤል አለምሸት በበኩላቸው "በአክሱምና አካባቢው ትልቅ የቅርስ ሃብት ቢኖርም ከቱሪዝም መገኘት የሚገባው ገቢ እየተገኘ አይደለም" ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በአካባቢው ያሉ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ በማልማት እና መረጃዎችን በጽሁፍ በማደራጀት በኩል የበኩሉን እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። እንደ መምህሩ ገለጻ በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የሚገኙ የአቡነ ጰንጠሊዎን ገዳምን ጨምሮ በዓዲ ጸሐፊና ሰግላሚን አካባቢዎች የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን የማስተዋወቁ ሥራ እስካሁን ድረስ ትኩረት አልተሰጠውም። የላዕላይ ማይጨው ወረዳ አስተዳደር ራሱን የቻለ የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት እንደሌለውና በወረዳዋ ያሉ ቅርሶች በአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ስር እንደሚተዳደሩ የተናገሩት ደግሞ የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹምብርሃን ናቸው። ጽህፈት ቤቱ ካለው በጀት እና የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት በወረዳው የሚገኙ ቅርሶችን በሚገባ ማስተዋወቅ እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመተባበር ወደ ገዳሙ የሚወስድ የጠጠር መንገድ ለመስራትና በገዳሙና በአካባቢው ያሉ ቅርሶችን ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በገዳሙ የሚገኙ ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ወጪ በማድረግ ባለፈው ዓመት በገዳሙ ውስጥ ሙዚየም አስገንብቶ ጥቅም ላይ ማዋሉን ተናግረዋል። ጽሕፈት ቤቱ ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩትን የአጼ ካሌብና የአጼ ገብረመስቀል መቃብር መጠገኑንም ገልጸዋል። በቀጣይ በአክሱምና በአካባቢው ያሉ ቅርሶችን በሚገባ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም