የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የግንባታ እቃዎች ስርቆት እየተፈፀመባቸው ነው

መስከረም 22/2012 የአዋሽ-ኮምቦልቻ -ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦት በወቅቱ ባለማግኘቱ ለግንባታው በቀረቡ እቃዎች ስርቆት እንዲፈጸምባቸው ምክንያት ሆኗል ተባለ። የግንባታ ቁሳቁሶች ስርቆቱ እየተፈፀመ ያለው በባቡር መስመሩ ምዕራፍ አንድ ላይ ሲሆን የኃይል እጦት ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ተጠቅሷል። በ2007 ዓ.ም መጨረሻ በሁለት የግንባታ ምዕራፍ ስራው የተጀመረው ይህ የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፉ 99 በመቶ መጠናቀቁ ተገልጿል። ግንባታውን በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ዛሬም በተለያዩ ምክንያቶች ሊጠናቀቅ እንዳልቻለ ነው የተነገረው። የፕሮጀክቱ የኃይል አቅርቦት ክፍል ምክትል ኃላፊ አቶ ባበይ በዛብህ ለኢዜአ እንደተናገሩት 99 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው ምዕራፍ አንድ አሁን ባለበት ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ይችላል። ሆኖም የባቡር መስመሩ ኃይል ባለማግኘቱ ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዳይሄድ እንዳደረገው አስረድተዋል። የመስመሩ ኃይል አለማግኘት ባቡሩን ከኃይል በሚያገናኙ መስመሮች፣ ስልኮች፤ ብሎኖችና የባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት እየተፈፀመና ለተጨማሪ ጊዜና ወጪ እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል። የባቡሩን ሃዲድ ለመዘርጋት ጥቅም ላይ የዋሉና እየተዘረፉ ያሉት መሳሪያዎች ከውጭ አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተገዙ መሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው አክለዋል። ባቡሩን ከኃይል የሚያገናኙ 37 ሺህ ሜትር ሽቦዎች፣ ከባቡር ጣቢያዎች ጋር የሚያገናኙና በመሬት ውስጥ የተዘረጉ 46 መስመሮችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ንብረቶች መሰረቃቸውንም ጠቁመዋል። ለግንባታው ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙት እቃዎች ጥራት ጋር ተያይዞ የተሰረቀው ንብረት ወደ ገንዘብ ሲቀየር በሚሊዮን የሚገመት ዶላር መሆኑን አቶ ባበይ ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ የኃይል አቅርቦቱ በወቅቱ ቢገኝ በመስመሩ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስርቆት  በመቀነስ ወደ አገልግሎት ማስገባት ይቻላል። ችግሩን ለመፍታት ከአካባቢው የጸጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ስርቆቱን ለማስቆም የኃይል አቅርቦት ችግሩን መፍታት ዋነኛው አማራጭ ነው ብለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የችግሩን ፈጻሚዎች በመያዝ ለህግ አካላት እያሳወቁ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢያደርጉም ብዙም ሳይቆዩ እንደሚለቀቁ ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የባቡር መስመሩ ዝርጋታ ያለበትን ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሲያስጎበኝ በመሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ዝርፊያ መታዘብ ተችሏል። በጉብኝቱ ወቅት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የምዕራፍ ሁለት ግንባታ 70 በመቶ መድረሱም ተገልጿል። ፕሮጀክቱ 390 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ 'ያፒ መርከዚ' በተሰኘ የቱርክ ግንባታ ተቋራጭና በኢትዮጵያዊያንና በፈረንሣዊያን አማካሪዎች በመገንባት ላይ ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት 65 ድልድዮችና 10 የባቡር ጣቢያዎች፣ 8 የኃይል አቅርቦት ጣቢያዎችና 824 ሜትር ኪውቢክ የአፈር ቆረጣ ስራዎችን ያካተተ ሲሆን ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮችን ያስተናግዳል ተብሏል። የባቡር መስመሩ ዝርጋታ ሲጠናቀቅ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳልጥም እምነት ተጥሎበታል። በኢትዮጵያ ምድር ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በሰሜን ኢትዮጵያ አቅጣጫ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመሩ ከአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ተነስቶ በአዋሽ አርባና በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ ሐይቅ፣ መርሳና ሌሎች ከተሞችን አቋርጦ እስከ ወልድያ/ሃራ ገበያ የሚዘልቅ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም