ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአለም አቀፉን የሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ህብረት ሲንፖዚየም ልታስተናግድ ነው

መስከረም 21/2012 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ህብረት ሲንፖዚየምን ልታስተናግድ ነው። ሲምፖዚየሙ ከመጪው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጰያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት ዛሬ ለኢዜአ ገልጿል። ከጥንታዊ ሳይንሶች አንዱ የሆነው ሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ከመሬት ከባቢ አየር ውጪ የሚገኙ ክስተቶችን የሚያጠና የሳይንስ ክፍል ሲሆን ፀሐይ፣ የከዋክብትና የጨረቃዎች ስርዓት ማለት ነው። ሲንፖዚየሙ የኢትዮጰያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከምስራቅ አፍሪካ አስትሮኖሚ ለልማት ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን እንደሚካሄድ ተገልጿል። በምስራቅ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄደው ሲንፖዚየም ከ30 አገራት የተውጣጡ ወደ 160 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች፣ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችና ባለ ድርሻ አካላት ይሳተፉበታል። ሲንፖዚየሙ በአገሪቱ መካሄዱ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ላይ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ልምድ ለማግኘት እድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል። አለም አቀፍ የሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚካል) ህብረት 100ኛ ዓመት እየተከበረ እንደሚገኝም ተገልፇል። ዓመቱ በኢትዮጵያም ስለየሥነ ፈለክ ሳይንስ ግንዛቤ በሚፈጥሩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን ነው መግለጫው ያመለከተው። ሲንፖዚየሙ ከመካሄዱ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች እና በአስር የህዝብ ትምህርት ቤቶች በተግባር የታገዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ተገልጿል። ከሲንፕዚየሙ ቀጥሎም ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ስልጠና እንደሚሰጥም እንዲሁ። ከሲንፓዚየሙ ጎን ለጎን የሥነ ፈለክ ሳይንስ በአፍሪካ እንዲያድግ ስትራቴጂ ይቀረጽበታል ተብሎ የሚጠበቅ የአፍሪካ የሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚካል) ማህበር ውይይት እንደሚካሄድም ተገልጿል። ውይይቱ የሥነ ፈለክ ሳይንስ በአፍሪካ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚያስችልም ነው የተጠቀሰው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም