የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለክልሉ ሰላም ጉልህ ድራሻ አለው...የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለክልሉ ሰላም ጉልህ ድራሻ አለው...የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪዎች
ጎባ (ኢዜአ) መስከረም 21 ቀን 2012 በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው በክልሉ ሰላምን ቀጣይ ለማድረግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የፓርቲዎቹ ስምምነት ከኦሮሚያ አልፎ በሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ተሞኩሮ እንደሚሆንና የሰለጠና የፖለቲካ አካሄድ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የፓርቲዎቹን ስምምነት አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው የባሌ ሮቤ ከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀሰን መሀመድ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ነበሩ። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በህዝብ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ከዚህ በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን በማስቀረት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። "ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆንም የሚጠበቅብኝን ለመወጣት እሰራለሁ" በማለት ነው የተናገሩት። ስምምነቱ በተለይ በተወሰኑ የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ በኦሮሞ ፓርቲዎች ስም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት በማስቀረት ሰላም እንዲሰፍን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ የሀገር ሽማግሌው አቶ ቃሲም ኢብራሂም ናቸው፡፡ "የተደረገውን ስምምነት እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመጠቀም የክልሉ ብሎም የአገሪቱ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በቀጣይ በሥራ ሂደት ለሚያጋጥማቸው ችግሮች መፍትሄ የሚያፈላልግና የኦሮሞ አመራሮችን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ "ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ" እንዲመሰረት መስማማታቸው አግባብ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ አቶ ከዲር ሁሴን የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ ናቸው። "ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ ችግሮችን በሰለጠና አግባብ ለመፍታት ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ስምምነቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል" ሲሉ ተናግረዋል። ፓርቲዎቹ በአሁኑ ወቅት የደረሱበት ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸውን ማስገንዘብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ "የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመካከላቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰለጠና አግባብ ለመፍታትና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስማማታቸው በክልሉየተጀመሩ ሁለንተናዊ ውጥኖች ከግብ እንዲደርሱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ያለው ደግሞ ወጣት አብዲሳ ገመቹ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ ኃይል ከስሜት ነፃ በመሆን አሁን የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ በመደማመጥና በመደጋገፍ የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያመለከተው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት መስማማታቸው ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ለተግባራዊነቱ ሁሉም አካላት ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል። የኢህአዴግ እና የኦዲፒ ሊቀ መንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የመድረክ እና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዲሁም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጋራ ለመስራት ትናንት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡