በምስራቅ ጎጃም ዞን በደረሰ የትራ ፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ሀይዎት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በደረሰ የትራ ፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ሀይዎት አለፈ
መስከረም 21/2012 በምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅ እናውጋ ወረዳ ዛሬ ረፋድ ላይ መንገድ ስቶ የወጣ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በስድስት ሰዎች ላይ የሞት አደጋ ማስከተሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የተከሰተው ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በወረዳው ፈለገ ብቸና ተብላ በምትጠራው ቀበሌ ነው። አደጋው የደረሰው ከባህር ዳር አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ ኮድ 3 20651 አ.ማ የሆነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ መንገድ ስቶ በመውጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚሁ አደጋም ወደ ገበያ ይሄዱ የነበሩና ከመንገዱ ዳር በሚገኝ ወንዝ እግራቸውን ይታጠቡ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ህይዎታቸው ማለፉን ጠቅሰው፤ በተሳፋሪዎች ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል። በደረሰው የትራፊክ አደጋም የአንዲት የሁለት ዓመት ህጻን ጨምሮ ስድስቱም ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አመልክተው፤ አደጋውን ያደረሰው አሽከርካሪ ለጊዜው በመሰወሩ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።