ቀጥታ፡

የኢሬቻ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በዓሉ የሰላም ምልክት መሆኑን ማሳየት ይገባል ተባለ

መስከረም 21/2012 የኢሬቻ በዓልን በተባበሩት መንግስትታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በዓሉ የሰላም ምልክት መሆኑን በተግባር ማሳየት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑ ተገለፀ። የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 እና 25 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከተሞች ይከበራል። በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በየዓመቱ ለሁለት ጊዜ የሚከበረው ኢሬቻ በዓል የምስጋናና የእርቅ በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። ኢሬቻ ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊሳተፍበት የሚችል፤ የሰላምና አብሮነት ተምሳሌት የሆነ በዓል መሆኑን አባገዳዎችና በመስኩ ጥናት ያካሄዱ የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ይገልፃሉ። በመሆኑም በዓሉ በህዝቦች መካከል መቀራረብን፣ ፍቅርንና እርቅን ለማምጣት የሚያግስ እሴት ያለው በመሆኑ በሁሉም ዘንድ እውቅናና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባም በማከል። ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ በዓሉ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ማድረግ አንዱ መንገድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ ለኢዜአ ገልፀዋል። እርሳቸው እንደሚሉት "ኢሬቻ ሰዎች ፈጣሪን ለጥሩ ነገር የሚማፀኑበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት የሰላም ምልክት" ነው። "ከበዓሉ እርቅን፣ ይቅር ባይነትንና አብሮነትን እንማርበታለን" የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ ይህ እሴት ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጠው የሰላም ምልክት ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊያን ይህንን የበዓሉን እሴቶች በተግባር በማሳየት ለዓለም ማስተጋባት አለባቸው፤ ይህም በዓሉ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ  ያግዛል ብለዋል። ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነው አቶ ተስፋዬ ጀቤሳ በበኩላቸው "ኢሬቻን አብረን ማክበራችን እርስ በእርስ እንድንተዋወቅና እንድንቀራረብ የሚያደርግ ነው" ይላሉ። በተለይም ዘንድሮ በዓሉ በአዲስ አበባ እንዲከበር መደረጉ እርስ በርስ ለመተዋወቅና ለመቀራረብ ያለው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው ሲሉም አክለዋል። "ልክ እንደሌሎቹ በዓላት ሁሉ አብረን በማክበር አንድነታችንን ማሳየት አለብን" ብለዋል። ኢሬቻ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ሁሉ በዓለም ቅርስነት እንደሚመዘገብ አልጠራጠርም የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ ይህ እንዲሆን ግን ሁሉም ዜጎች በዓሉ የሰላም ምልክት መሆኑን በተግባር ለማሳዬት መጣር አለብን ሲሉም ተናግረዋል። የኢሬቻ በዓል በየዓመቱ ለሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን የመጀመሪያው ክረምት መውጣትን ተከትሎ በውሃማ አካባቢዎች፤  ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ አካባቢዎች ይከበራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም