ቀጥታ፡

በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ22 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል

መስከረም 21/2012 በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ22 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የተከናወነው የበጎ ፍቃድ ተግባር በገንዘብ ሲተመን 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሆኑም ተጠቅሷል። ባለፉት የክረምት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መጠናቀቅን  በተመለከተ የተዘጋጀ ልዩ መርሃ ግብር ነገ ይከናወናል ተብሏል። መርሃ ግብሩን በተመለከተ የሴቶች፣ የህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በሰጡት መግለጫ በክረምቱ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የልማት ተግባራት ተከናውነዋል። ወጣቶቹ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በጤና፣ በማህበራዊ ደህንነት፣ በትራፊክ መንገድ ደህንነት፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ እንደዚሁም አረጋዊያንንና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ ተግባራት ተሳትፈዋል። በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 13 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች መሳተፋቸውንም  ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልፀዋል። በበጎ ፍቃድ ተግባሩም ከ22 ሚሊዮን የሚበልጥ የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ በማከል። የተከናወነው የበጎ ፍቃድ ተግባር በገንዘብ ሲተመን 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሆኑም ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ የወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጽጌሬዳ ዘውዱ በበኩሏ ወጣቶቹ ለበጎ አገልግሎት ተግባር ያላቸው ግንዛቤ በመጨመሩ በዘንድሮው ክረምት ከሌላው ጊዜ የተሻለ  ውጤት መመዝገቡን አንስታለች። የበጎ ተግባር መርሃ ግብሩ ወጣቱ ለአገሪቱ የልማት እድገት አለኝታ መሆኑን ያሳየበት መሆኑንም ገልፀዋል። እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት በሚኖርበት አገር ሁሉም ተግባር በመንግስት ብቻ ሊከናወን አይችልም ያለችው ምክትል ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለዚህ በጎ ተግባር በመሰለፋቸው ይህ ስኬት ሊመዘገብ መቻሉን ተናግራለች። ወጣቶቹ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ተግባር ጭምር ማከናወናቸውን ሚኒስትር ዲኤታዋ አመልክተዋል፤ በዚህ የበጎ አድራጎት ተግባር ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶች በድሬደዋ የተከሰተውን የችኩንጉንያ ወረርሽኝ ለመከላከል በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ በሰፊው መሳተፋቸውን አመልክተዋል። ይህም በተለያዩት የኢትዮጵያ ክልሎች ህዝቦች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል። የበጎ አድራጎት ተግባሩ በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በኩል ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ሲሆን የወጣቶቹ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስትር ዲኤታዋ ወይዘሮ ወይዘሮ ህይወት ገልፀዋል። የበጎ አገልግሎት ለአገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት የጎላ ሚና ያለው በመሆኑ በኢትዮጵያ ተግባሩን በዘላቂነት ለማስቀጠልም ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል። ወጣቶቹ የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። በዘንድሮው የበጎ አገልግሎት ተግባር ለተሳተፉት ወጣቶች በነገው እለት የማጠቃለያና የእውቅና መርሃ ግብር የሚከናወን መሆኑም ተጠቅሷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም