የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ የአጋር አካላት ትብብር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ የአጋር አካላት ትብብር ተጠየቀ
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 20/2012 የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ የአጋር አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠየቁ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን በዘርፉ ባሉት ምቹ የትብብር መስኮች ላይ በአዲስ አበባ መክሯል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ለትምህርቱ ዘርፉ በተለይም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥቷል። ለዚህም ደግሞ የአገሪቷ ችግሮች ከሞላ ጎደል የሚገናኙት ከድህነትና ከትምህርት አለመዳረስ ጋር መሆኑን ከግምት በማስገባት ለዘርፉ አጽንዖት መሰጠቱን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት አገሪቷ በተለይም አጋር አካላትን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ ትብብር እንዲያደርጉና ዘርፉን ውጤታማ እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸዋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የሰው ኃይል ኃብት እንዳላት ጠቁመው ይህንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማምጣትም አጋርነቱ ወሳኝ ነው ብለዋል። ትብብሩም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ ቁልፍ ችግሮች ላይ ያተኮረ የቅንጅት ሥራ መሆን እንዳለበትም አጽንጾት ሰጥተዋል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፋዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ይህም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋትን ተከትሎ የትምህርት መሳሪያ አቅርቦትና የመምህራን ቁጥር እንዲሁም የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ተነስተዋል ብለዋል። ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም ከሚፈለገው በታች በመሆኑ ተቋማቱ በምርምር ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል። ስለዚህም ከአጋር አካላት በፋይናንስ፣ በሥርዓተ-ትምህርት ክለሳ፣ በተቋማት አመራር ማዘመንና በመምህራን አቅም ማጎልበት ድጋፍ እንፈልጋለን ብለዋል። ጎን ለጎንም በሥልጠናና መሰል ሙያዊ ድጋፎች፣ በጋራ የዲግሪ መርኃ ግብሮችና በሌሎችም ምቹ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ፍላጎት አንዳለ ጠቁመዋል። ይህንንም ማድረግ ከተቻለ የትምህርትን ጥራት ማረጋገጥ እንደሚቻልና ተቋማቱንም ዓለም አቀፍ ገጽታ ማላበስ እንደሚቻል ነው የገለጹት ሚኒስትሯ። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ለመደገፍ በርካታ የድጋፍ ሥራዎች እየሰራን ነው ብለዋል። ባለፉት አስር ዓመታትም ከገንዘብና ከሙያዊ ድጋፍ ውጪ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል። አሁንም የትብብር አድማሱን ለማስፋትና ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 50 የመንግሥትና 201 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ። በእነዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይገኛሉ።