ቀጥታ፡

ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያቀረበችው ሀሳብ አገሪቱ በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ ከምታራምደው ያለመተማመን መንፈስ የመነጨ ነው

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 20/2012 ሰሞኑን በካይሮ ተካሂዶ በነበረው የሶስትዮሽ ስብሰባ ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያቀረበችው ‘’የተናጠል የውሃ አሞላል እቅድ’’ አገሪቱ የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ያለመተማመን መንፈስ ውጤት ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በቅርቡ በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ አዲስ ምክረ ሀሳብ አቅርባ ነበር። ግብጽ ያቀረበችው ምክረ ሀሳብ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እንዲሁም የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ የግድቡ ዋና ስራ ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚል ነው። ይህ በግብፅ በኩል የቀረበው የተናጠል እቅድ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መሪዎች መካከል ከተፈረመው የመርህ ስምምነት ውጪ መሆኑን ነው ባለሙያዎቹ የተናገሩት። በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ኢትዮጵያና ግብጽ ለረጅም ዓመታት ባለመተማመንና በጥርጣሬ ሲተያዩ ቆይተዋል። ይህ አለመተማመን የመጣው ደግሞ ግብጽ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት በመገደብ ‘እኔ ብቻ በውሃው ልጠቀም’ በሚል አቋሟ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር አንስቶ የግብጽ ጥርጣሬ እየተባባሰ ከመምጣት ባለፈ ግድቡ ‘በአገሪቷ ህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ’ መሆኑን ስትገልጽም ቆይታለች። በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የአህጉራቀፍና ዓለምአቀፍ ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን፤ ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ የበላይነቷን ለማረጋገጥ ስትንቀሳቀስ ኖራለች፤ ኢትዮጵያ ከግብጽ እውቅና ውጭ በወንዙ የመጠቀም መብት እንደሌላት የሚያንፀባርቅ አቋምም ስታራምድ ቆይታለች ይላሉ። በዚህም የተነሳ የአገራቱ ግንኙነት አንዳንዴ የተሻለ መልክ የሚያሳይ ቢሆንም ሌላ ጊዜ ደግሞ ግንኙነቱ ወደ ተካረረ ደረጃ ይደርሳል ሲሉ የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ በበኩላቸው ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያቱ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የቆየው ከፍተኛ አለመተማመን መሆኑን በመጠቆም። በአገራቱ መካከል ያለውን አለመተማመን ለመፍታትም ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እኤአ በ2015 የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ በመሪዎቻቸው ደረጃ የትብብር መርህ ስምምነት ተፈራርመዋል። የትብብር መርህ ስምምነቱ ዋና ዓላማ አንዱ አገር የሌላውን ጥቅምና ፍላጎት በማጤን አንዱ በሌላው ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ሉዓላዊነቱን ሳይጋፋ የወንዙን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም ነው። በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጊካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የአህጉራቀፍና ዓለምአቀፍ ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን እንደሚሉት የመርህ ስምምነቱ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ህጋዊ መብቷን ያረጋገጠችበት ነው። በመርህ ስምምነቱ መሰረት ከሶስቱም አገሮች የተወጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴ ተቋቁሞ በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ጥናትና ምርምሮችን ሲያያካሄዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ይሁንና በቅርቡ በግብጽ ካይሮ በተካሄደው የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ውይይት ላይ ግብጽ ይዛ የቀረበችው የተናጠል የውሃ ሙሌት እቅድ አገሪቷ ‘የአባይን ውሃ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የረጅም ጊዜ አመለካከቷ ውጤት ነው’ ይላሉ። እቅዱ ቀደም ሲል በመሪዎች ደረጃ የተፈረመውን የመርህ ስምምነት የጣሰ መሆኑ በማስረዳት። የግብጽ መሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ አሉታዊ ሀሳቦችን በማንሳት ግንባታውን ለማስተጓጎል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል። የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንደሚሉት አንድ አገር በድንበሩ ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም ህጋዊ መብት አለው። ይሁንና ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ይዛው የመጣችው አዲስ እቅድ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን የሚነፍግ ነው። ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች በማይጎዳና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ ቢሆንም በግብጽ በኩል ግን እየተሰጣት ያለው ምላሽ አሉታዊ መሆኑን በማንሳት። ኢትዮጵያ ግድቡን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በውሃ መሙላትና መጠቀም የምትችል ቢሆንም የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ጊዜውን ማራዘሟን አንስተዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓመት ከ29 እስከ 30 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመልቀቅ አቅም እንዳላት ያብራራሉ። ያለዚያ ግን እንደ ግብጽ ፍላጎት በዓመት 40 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜተር ውሃ መልቀቅ ግድቡ ዕድሜ ልኩን ውሃ አይሞላም ማለት ነው ሲሉም በማከል። የግብጽን ጥርጣሬ ለመቀነስ የዘርፉ ምሁራን ዓለምአቀፍ የውሃ ህጎች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ምክረ ሀሳቦችን ሊያቀርቡ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋ። ኢትዮጵያ እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኮንጎና ሌሎችም የላይኛው የፋሰስ አገሮች ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል። የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ከ68 በመቶ በላይ ሥራው ተጠናቋል። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ ሜጋዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም