ቀጥታ፡

ጉባኤው በሃይማኖት ሽፋን የሚደረግ የግጭትና የጥላቻ ቅስቀሳን አወገዘ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 20/2012 በሃይማኖት ስም በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎች መንገዶች በተለያዩ አካላት የሚካሄደው የግጭትና ጥላቻ ቅስቀሳ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለው የተወገዘ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ። ጉባኤው በሠላምና በመከባበር ዕሴት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አስታውቋል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 11ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል። በዚሁ ወቅት የጉባኤው ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ብፁዑ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘ ኢትዮጵያ ተወካይ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ባስተላለፉት መልዕክት የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ለአገር ሰላምና እድገት ግንባር ቀደም ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአባላቱ የተጣለበትን ሀገራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ተናግረዋል። ጉባኤው በተለይም በሰላምና በመከባበር እሴት ግንባታ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ይበልጥ ወደ ህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል። ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የቆየው ሰላምና አብሮ የመኖር የጋራ ዕሴት እንዲቀጥል ቃል ኪዳን የሚገባበት ነው ሲሉም ገልፀዋል። "ስለሆነም እኛ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሃይማኖትንና እውነተኝነትን ወደ ሕዝባችን ለማስረጽና የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በፍጹም መዋደድና መከባበር እንዲኖሩ ራሳችንን አርአያ ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል። የጉባኤው አባላት የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲቀጥል ማድረግ ከፈጣሪም ሆነ ተቋማቱ ከሚያገለግሉት ምዕመን የተጣለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት ነው ሲሉም ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከዚህ ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ባፈነገጠ መንገድ በሃይማኖት ሽፋን በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎች ልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን እየተካሄደ ያለውን ቅስቀሳ አውግዘዋል። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን በሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት በጥልቅ መሠረት ላይ የተገነባ የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴት ባለቤት ናቸው ብለዋል። ይህንን ታላቅ አገራዊ እሴት ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ ተጠቃሚ መሆን ይቻል ዘንድ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ሆኖም እሴቱን የበለጠ ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግን ደግሞ ከሃይማኖቶች መሠረታዊ መርሆና አስተምሮት ጋር ተቃራኒ ተግባራትን የሚፈጽሙ ጽንፈኛ አካላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መታየት መጀመራቸውን ሚኒስትር ዲኤታዋ አስረድተዋል። "በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍል የሚታየው ችግር ከብሔርና ከማንነት ጉዳይ አልፎ ሃይማኖታዊ እንዲመስል በማድረግ አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳትና በመካከላቸው አለመተማመን ለመፍጠር በቤተ እምነቶች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርሱ ይስተዋላል" ሲሉም አክለዋል። ይህን ሁኔታ ይከሽፍ ዘንድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉበኤ አባላት ሀገራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትር ዲኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። ይህን የጋራ ኃላፊነት በጋራ ለማሳካት መንግሥት ከተቋሙ ጋር በትብብር እንደሚሠራም ወይዘሮ አልማዝ ቃል ገብተዋል። ለአንድ ቀን የቆየው ጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች በሃይማኖት ስም የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረትና የሀገሪቱን ሠላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ በየቤተ እምነቶቻቻው ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ቃል ገብተዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የጉባኤውን ያለፈ ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርትና የቀጣይ ዓመት የሥራ አቅጣጫ ለተወያዮቹ አቅርበው አፀድቀዋል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይም ከዚህ በፊት ተቋሙን ሲያገለግሉ ለነበሩ የቦርድ አመራርና የበላይ ጠባቂዎች የዕውቅናና የምስጋና ስጦታ ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም