በቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩት ባለሙያዎች 32 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሙያዊ ስልጠና ያገኙ መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩት ባለሙያዎች 32 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሙያዊ ስልጠና ያገኙ መሆናቸው ተገለጸ
መስከረም 20/2012 በቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩት ባለሙያዎች 32 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሙያዊ ስልጠና ያገኙ መሆናቸው አንድ ጥናት ይፋ አደረገ። ይህ የተገለጸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከድሬዳዋ ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የቱሪዝም ሳምንት ክብረ በዓል ላይ በቀረበ ጥናት ነው። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያ አቶ ማዘንጊያ ሽመልስ ባቀረቡት ጥናት እንዳመለከቱት "በአገሪቱ ካለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የሰለጠነ የሰው ሃይል በዘርፉ አልተሰማራም።" በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት ባለሙያዎች በቂ ልምድና ከህሎት እንደሌላቸው ገልጸዋል። በቂ ስልጠና ከወሰዱት መካከልም 85 በመቶ የሚጠጉት የብቃት መመዘኛ ፈተና ማለፍ እንዳልቻሉ በጥናታቸው አመላክተዋል። በዘርፉ የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ሰራተኞች የትምህርት ደረጃም ከ12 ኛ ክፍል ያልዘለለ መሆኑን ጠቅሰው ምክንያቱ ደግሞ በቂ የሆነ የማሰልጠኛ ማዕከላት አለመኖርና የተግባር ስልጠና በመስጠት በኩል ክፍተት በመኖሩ ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሆቴል ዘርፉ የስራ ቅጥር በአብዛኛው በዘመድ ስለሚፈጸም ስልጠና የወሰዱትም ቢሆኑ በበቂ ደረጃ በስራው ላይ አለመሰማራታቸውን ጠቁመዋል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ለባለሙያዎቹ በክህሎትና በልምድ የታገዘ ስልጠና መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል። የባህልና ቱሪዝም የስልጠና ማዕከላትን በማስፋፋትና ዘመናዊ የአሰራር ዘዴን በመከተል ኢንዱስትሪውን ማሳደግ እንደሚቻል በመጠቆም። የኢትዮጵያ ሆቴሎችና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በበኩላቸው ጥናቱ በዘርፉ ያለውን ክፍተት የሚያመላከት መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የሰለጠነ የሰው ሃይል በማግኘት በኩል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል። ዘርፉን ለማሳደግ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመናበብ እንደሚሰሩ ገልጸው የማሰልጠኛ ተቋማቱን የስልጠና ሂደት ለማዘመን የሚረዳ ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል። የቱሪዝም ዘርፉ የስራ ዕድል በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወት ስለሚችልም በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ተገልጿል። "ቱሪዝም ለስራ ዕድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት" በሚል መሪ ቃል ሐሳብ በድሬዳዋ ከተማ አዘጋጅነት ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው በዓል ዛሬ ተጠናቋል። በዓሉ በአለም ለ40 ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32 ኛ ጊዜ ተከብሯል።