ቀጥታ፡

የእንስሳት ሃብት ተዋጽኦ አውደ ርዕይ ከጥቅምት 6 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል

መስከረም 20/2012 በኢትዮጵያ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም የአገር ውስጥ ምርት አቅርቦት በሚፈለገው መጠንና ጥራት ማዳረስ እንዳልተቻለ ተገለጸ። በፕራና ኢቨንትስ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚካሄደውን የእንስሳት ሀብት ትርኢትና ዐውደ ርዕይ አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል። በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው በዚሁ የእንስሳት ሃብት ትርኢትና አውደ ርዕይ የዘርፉን ዋነኛ አንቀሳቃሾችን በማሳተፍና ከአስር ሃገራት የተውጣጡ ከአንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል። በዚህም ከ4ሺህ ታዳሚዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅም የዐውደ ርዕዩ አዘጋጅ የፕራና ኢቨንትስ ቴክኖሎጂ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ለማ ተናግረዋል። በንግድ ትርኢቱ፣ ዐውደ ርዕዩና በፎረሙ ከሚሳተፉትም የኢትዮ-ፖሊተሪ ኤክስፖ፣ የአፍሪካ እንስሳት አውደ ርዕይና ጉባኤ እንዲሁም የአኳ ካልቸር እና አፒ ካልቸር ኢትዮጵያ እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ይገኙበታል። በግብርና ሚኒስቴር የገበያ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ አዲሱ ስሜ እንዳሉት የዚህ አይነቱ ዐውደ ርዕይ በአገራችን መካሄዱ ከባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመገናኘትና በመምከር የገበያ ትስስሩን አስተማማኝ ከማድረጉም በላይ አርሶ አደሩ ወይም አርብቶ አደሩንም ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በአገሪቷ ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደነበርና በእንስሳት ንግድ ላይ መቀዛቀዝን ፈጥሮ የነበረ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው አሁን ግን በአገሪቷ የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩ አገር አቋራጭና ህገወጥ የእንስሳት ንግድ ላይ ቁጥጥሩን በማጥበቅ ወደ ቀድሞው መልኩ ለመመለስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ገነነ ተስፋዬም አቅም የሌላቸው ግን ወደዚህ የንግድ ዘርፍ እየገቡ ያሉ ጀማሪ ነጋዴዎች የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያገኙ እንደሚረዳ ገልጸዋል። አክለውም ህገወጥ እርድንና የኮንትሮባንድ የእንስሳት ንግድን በማስቆም ወጣቶችን ወደስራ ለማስገባትም ሰፊ የስራ ዘርፍ ያለውና በአገሪቷ እየታየ ያለውን የስራ አጥነት ችግር የሚፈታ በመሆኑም መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የቁም ከብቶች የላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተፈራ ሃይሉ በበኩላቸው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በአገር ውስጥ ያልተለመዱና ለአገር ውስጥ ገበያ የማይውሉ የስጋ ምርቶች በመሆናቸው በአገሪቷ ያለውን የእንስሳት ምርት ዋጋ ገበያ ሊያንረው እንደማይችል ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የእንስሳት ምርት አቅራቢዎች አብዛኛው አርቢዎች ሳይሆኑ ለትርፍ ገዝተው የሚሸጡት ስለሚበረክቱ ገበያው እየጨመረ የመጣው የአርብቶ አደሩ ቁጥር አናሳ መሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም