ቀጥታ፡

ወባን በመከላከል የተመዘገበው ለውጥ በማጥፋትም ሊደገም ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

መስከረም 20/2012 በኢትዮጵያ ወባን በመከላከል የተመዘገበው ለውጥ በማጥፋትም ሊደገም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር እስከ 2030 ወባን የማጥፋት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ሲከወን ነው። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ይያዛሉ፤ በየሁለት ደቂቃውም አንድ ህፃን ይሞታል። በኢትዮጵያም መንግስት የወባ በሽታን መከላከል በመቻሉ ባለፉት 15 ዓመታት ምንም አይነት የወባ ወረርሽኝ ባይከሰትም ከአስሩ ገዳይ በሽታዎች አንዱ ነው። በ2011 ዓ.ም ብቻ 900 ሺህ ዜጎች በወባ የተያዙ ሲሆን፣ በየደቂቃውም ሁለት ሰዎች በወባ ይታመማሉ። "ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" የሚል መሪ ሃሳብ ባለው ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች፣ አምባሳደሮችና የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል። እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ገለጻ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ወባን በመከላከል ስራ ስኬታማ ሆናለች። 'ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ባደረግነው ወባን የመከላከል እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተናል' ብለዋል። በቀጣይም በአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ መሰረት እ.አ.አ 2030 ወባን ለማጥፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ 'ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ሆና ትቀጥላለች' ነው ያሉት። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወባን በመከላከል የተመዘገበውን ለውጥ ከአገሪቱ ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ልንደግመው ይገባል ብለዋል። "ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል፤ እኔም የንቅናቄው አካል ነኝ" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ለዚህ ስኬት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ሁሉም አካል በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የአገሪቱን 279 ወረዳዎች ከወባ ነፃ እናደርጋለን ብለዋል። ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ 70 በመቶ የቆዳ ሽፋንና 60 በመቶ ህዝብ የሚኖርባቸው ክፍሎች የወባ በሽታ የሚከሰትባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል። 'በትብብር ከሰራን ከ12 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ከወባ ነፃ የማድረግ ዘመቻው እውን ይሆናል ብለዋል ዶክተር አሚር። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር የወባ በሽታ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ተናግረዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ወባን በመከላከል ያስመዘገበችው ውጤት በማጥፋትም እውን እንዲሆን አሜሪካ በትብብር ትሰራለች ብለዋል። አሜሪካ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወባን ለመከላከል የሚውል 442 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ማድረጓን አውስተዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ ወባን ለማጥፋት በምታደርገው ርብርብ አሜሪካ ትብብር እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም