በኔትወርክ መቆራረጥ ሳቢያ አገልግሎት ሳናገኝ ለመመላለስና ለእንግልት ተዳርገናል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኔትወርክ መቆራረጥ ሳቢያ አገልግሎት ሳናገኝ ለመመላለስና ለእንግልት ተዳርገናል-ነዋሪዎች
መስከረም 20/2012 የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ወረዳዎች በምንሄድበት ወቅት 'ኔትወርክ የለም' በሚል ለእንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። የጽሕፈት ቤቶቹ ኃላፊዎች በበኩላቸው የዲጂታል አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ እየተፈጠረ ያለ የኔትወርክ መቆራረጥ መኖሩን ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን ሲገልፁ የከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። በመዲናዋ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ስራውን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አገልግሎት መተግበር ጀምሯል። በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የዲጂታል መታወቂያ አሰጣጥም የዚህ ዘመናዊ አሰራር አካል ሲሆን እስካሁን ባለው በከተማዋ ባሉ 49 ወረዳዎች እየተተገበረ እንደሚገኝም ተገልጿል። ሆኖም የዲጂታል መታወቂያ መሰጠት ከጀመረ በኋላ ለአገልግሎት ወደ ወረዳ ሲሄዱ ኔትወርክ የለም በሚል ለምልልስና እንግልት እንደተዳረጉ ነዋሪዎች ያማርራሉ። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እና 10 ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አገልግሎት ለማግኘት ሲያቀኑ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተናግረዋል ። ነዋሪዎቹ አክለውም የሰራተኞችን ቁጥር በማሳደግና የኔትወርኩንም ችግር በመፍታት ቀልጣፋ መስተንግዶ ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የወሳኝ ኩነት የማስረጃ ባለሙያው አቶ የኑስ ደሴ የኔትወርኩ መቆራረጥ ከሰራተኛው ቁጥር ማነስ ጋር ተደምሮ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ እንዳረጋቸው ያነሳሉ። ችግሩን ለበላይ አካል ማሳወቃቸውን በማውሳት። የወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸናፊ መርጋ በበኩላቸው ወደ አዲስ አሰራር መገባቱ መልካም ቢሆንም ከኔትወርክ ጋር ተያይዞ እየገጠሙ ያሉ መቆራረጦች ማስቸገራቸውንና ይህንንም ለክፍለ ከተማውና ለከተማው አመራሮች ማሳወቃቸውን አብራርተዋል። የወረዳ 10 የወሳኝ ኩነት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አለም አዲስም የሰራተኛ ችግር በእነሱ ወረዳ ላይ ባይኖርም ከኔትወርክ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች እንዳሉና በአቅማቸው ልክ ለመፍታት እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንና በስራው መሃል እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። የወሳኝ ኩነት መረጃ ምዝገባና ማስረጃ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ አንተነህ ካሳ ዘርፉ አድካሚ ስራዎች የሚከወኑበት መሆኑን ገልፀው ሆኖም የሚከፈለው ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍልሰት እንዳለ ገልፀዋል። በኤጀንሲው የነዋሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት በቀለ እንደሚሉት ደግሞ በከተማዋ ካሉ ወረዳዎች ውስጥ በ49ኙ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በአገልግሎት ዙሪያ እየገጠሙ ያሉ ችግሮች እንዴት ይፈታሉ በሚለው ዙሪያም በየጊዜው ምክክር እየተደረገ ነው ብለዋል። የኤጀንሲው አማካሪ የሆኑት አቶ መላክ መኮንን በበኩላቸው የዲጂታል አገልግሎቱ የሚሰጠው በወረዳ ኔት በመሆኑና ተቋሙ የራሱ ሰርቨር የሌለው በመሆኑ የኔትወርክ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ይናገራሉ። ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ምክክር ከኢትዮ ቴሌኮምና መሰል ተቋማት ጋር እየተደረገ መሆኑን በማውሳት። ኤጀንሲው እስካሁን ባለው 45 ሺህ ዲጂታል መታወቂያዎችን ማተሙን ተናግረው የሲስተም መቆራረጥ ሲኖር የካርድ መታወቂያ እንዲሰጥም 1 ሺህ ያህል ካርዶች ታትመው ለወረዳዎች መሰራጨታቸውን ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በ2011 በጀት አመት 64 ሺህ 844 የልደት፣ 4 ሺህ 447 የሞት፣ 26 ሺህ 412 የጋብቻ እንዲሁም 2 ሺህ 80 የፍቺ ኩነቶች ተመዝግበዋል። በተጨማሪም 122 የጉዲፈቻ መረጃ መመዝገቡንና በአጠቃላይ በበጀት አመቱ የተመዘገቡ ኩነቶች 97 ሺህ 931 መሆኑንም ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።