ቀጥታ፡

ሸገርን የማስዋብ የግንባታ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 20/2012 በቻይና መንግስት ትብብር በአዲስ አበባ የሚገነባው የወንዝ ዳርቻ ልማት "ሸገርን የማስዋብ" ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተጀመረ። በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ  ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ  የቻይና መንግስት ተወካዮችም ተገኝተዋል። በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ መንግስት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ለማድረግ በገባው ቃል መሰረት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል። በዚሁ መሰረት ባለፈው  አንድ ዓመት  ከተጀመሩ በርካታ ሥራዎች መካከል ይሄኛው ፕሮጀክት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። የቤተመንግስት እድሳት፣ የሸገር ፕሮጀክት እንዲሁም ከቦሌ እስከ ቤተ መንግስት ያለው መንገድ በተለያዩ ዛፎችና መብራቶች እንዲደምቅ በማድረግ ከተማዋን እንደ ቤጂንግ እና ዱባይ ውብ ለማድረግም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ ከተማዋን እንደ ስሟ ለማድረግ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ ክፍት ከማድረጉም ባሻገር ጎብኝዎችን በመሳብ ነዋሪዎቿ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚረዳም ጭምር አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ምንም አይነት ኃይል ሊያስቆመው እንደማይችል በመግለጽ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚመኟት አገር እንደምትሆንም በእርግጠኝነት አንስተዋል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በበኩላቸው አዲስ አበባ በተራራ የተከበበችና በርካታ ወንዞች የሚፈሱባት ድንቅ ተፈጥሮ ያላት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል። ለአብነትም የእንጦጦ ተራራና የአቃቂ ወንዞችን ውበት ያነሱት አምባሳደሩ ይሄን በማልማት ለዓይን የሚማርክ ስፍራና ጎብኝዎችን መሳብ የሚችል ከባቢ መፍጠር እንደሚቻል አንስተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አነሳሽነት የተጀመረው ይሄ ፕሮጀክትን ጨምሮ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሞች ሲጠናቀቁ ከተማዋን እንደ ስሟ ከማድረግ ባሻገር የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ ጎብኝዎችን በመሳብ አስተዋፆ ይኖረዋልም ብለዋል። ቻይና ይሄ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ እንዲሆን እያገዘች መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ፕሮጀክቱንም ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በፊት ለማጠናቀቅ  ሌት ተቀን እንደሚሰራ ገልፀዋል። በፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ እስከ ባምቢስ ድልድይ ያለው 12 ኪሎ ሜትር ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻዎች የሚለማ ሲሆን ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬትም እንደሚለማም እንዲሁ። ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት የሚገነባው ግዙፍ ክፍት መዝናኛ እና አደባባይ የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊነት በሚገልፅ መልኩ እንደሚገነባም ተገልጿል። በግዙፉ ፓርክ ሰው ሰራሽ ሃይቅ፣ የሙዚቃ እና የተለያዩ ትርኢቶች መከወኛ ቦታ፣ የህፃናት መጫወቻ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሌጂ ማዕከል እንደሚኖሩ ተጠቁሟል። በቻይና መንግስት ድጋፍ የሚሰራው የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅና ስምንት ወራት ጊዜ እንደተሰጠውም ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም