ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ተጠያቂነት በተመለከተ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ  መስከረም  20 /2012 የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ተጠያቂነት በተመለከተ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው በፖሊሲው ላይ የሚመክርና የየአገራቱ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ አዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል። ውይይቱ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የሰው ኃብት አስተዳደር ፖሊሲው በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት የተጠንቀቅ ኃይሉ መውሰድ ያለበትን እርምጃ፣ የተልዕኮ ወሰን እና አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለውን መመሪያ ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ሚስተር አብዱላሂ ዑመር በውይይቱ መክፈቻ እንዳሉት ፖሊሲው አሁን ያለውን አሰራር ለማሻሻልና አባላቱ በግዳጅ ወቅት መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ በአግባቡ ተገንዝበው እንዲተገብሩ ያስችላቸዋል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የዚህ  ዓመት የአህጉሩ ተጠባባቂ ኃይል ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ ይህ ተግባር ለተንጠቀቅ ኃይሉ ወሳኝ ነው ብለዋል። አፍሪካ ህብረት በማንኛውም ወቅት የተጠንቀቅ ኃይሉን በመጥራት ለሚፈለገው ዓላማ ማሰማራት ይችላል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። ፖሊሲው የተጠንቀቅ ኃይሉን የግዳጅ ዓይነት፣ የተልእኮ ወሰንና ተጠያቂነትን የሚያካትት መሆኑም ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሲው የተጠንቀቅ ኃይሉ የሚሰጠውን ግዳጅ ህጋዊ መሰረት ለማስያዝም እንደሚያስችል ተናግረዋል። የፖሊሲ ሰነዱ ኤክስፓርቶቹ ውይይት ካደረጉበት በኋላ በየአገራቱ መከላከያ ሚኒስትሮች ምክክር ተደርጎበት በተያዘው የአውሮፓ ዓመት መጨረሻ ስራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ኤክስፓርቶች ውይይቱ ከዛሬ ጀምሮ ለ4 ቀናት ይቆያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም