''ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ይህን ድል በማስመዝገቤ ተደስቻለሁ’’ አትሌት ሙክታር እንድሪስ

አዲስ አበባ  መስከረም  20 /2012 ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ በኳታር ዶሃ ባስመዘገበው ድል መደሰቱን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ሙክታር እንድሪስ ተናገረ። በኳታር ዶሃ እየተካሄደ የሚገኘው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአራተኛ ቀን ውሎው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር አንደኛና ሁለተኛ በመሆን አሸንፈዋል። ያስመዘገቡትን ድል ተከትሎም ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት ደረጃዋን ወደ አምስተኛ ከፍ አደረጋለች። በውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ የ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን የቻለው አትሌት ሙክታር እንድሪስ ሲሆን አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አምጥቷል። በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሞፋራህ ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ ሞፋራህን አስከትሎ የገባው ሙክታር ትናንትናም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድሉን መድገም ችሏል። ሙክታር ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተየያት ''ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ይህን ድል በማስመዘገቤ ተደስቻለሁ’’ ሲል ተናግሯል። ከዓመት በፊት የቁርጭምጭሚት ጉዳት አጋጥሞት የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላም በሆድ ህመም ሳቢያ ከውድድር ርቆ ቆይቷል። ከጉዳቱ አገግሞ በትናንት ምሽቱ ውድድር በማሸነፉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ነው የገለጸው። ኢትዮጵያ በትናንቱ ድል በተገኙት አንድ የወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ ከነበረችበት 8ኛ ደረጃ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች። እስከ ትናንት ድረስ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ በተገኘው የብር ሜዳሊያ ስምንተኛ  ደረጃ ላይ ነበረች። በቀጣዮቹ ቀናት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድርን ጨምሮ በተለያዩ ርቀቶች እንደሚያሸንፉ ይጠበቃሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም