ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡን በማፈናቀል ተግባር የተሰማሩ ወገኖች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው - የኃይማኖት አባቶች

አዲሰ አበባ ሰኔ 8/2010 ከሕብረተሰቡ አብሮ የመኖር ባህል ጋር ፍጹም በመቃረን በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች ዜጎችን በማፈናቀል ተግባር የተሰማሩ ወገኖች ከድርጊታቸው መታቀብ እንዳለባቸው የኃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ። በአገሪቷ  ቀድሞ የነበረውን እንግዳ ተቀባይነትና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠል የአገር ሽማግሌዎችና ማሕበረሰቡ ከኃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል። ዜጎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ማፈናቀል በየትኛውም ኃይማኖት የሚወገዝ እንደሆነ ያመለከቱት የኃይማኖት አባቶች፤ በተሳሳተ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ፈጣሪያቸውን በመፍራት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ኑቡረእድ ኤልያስ አብርሃ ለኢዜአ ሲናገሩ "ክቡር የሆነው የሰውን ልጅ ማክበርና መውደድ ፈጣሪን ማክበርና መውደድ ነው" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የሚታየውን አለመግባባትና ግጭት በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና የዜጎችን ከቦታ ቦታ ማፈናቀል ለማስቆም የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በመተባበር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የቤተክስቲያኗ የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ሕብረተሰቡን በማፈናቀል ተግባር ላይ የተጠመዱ ወገኖች ፈጣሪያቸውን በመፍራት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ገልጸዋል። መንግስት ያሉትን ችግሮች በመፈተሽ መፍትሄ መስጠት እንደሚጠበቅበት የጠቆሙት አባ ሠረቀ፤ “የሃይማኖት አባቶችም በየቤተ እምነታቸው የሚገኙ ምእመናንን ለማስተማር ስራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእርዳታና ማሕበራዊ ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ ሐጂ ማሐሙድ ኡመር እንደሚሉት፤ በእስልምና እምነት አስተምሕሮ መሰረት ሰዎች ከኖሩበት ቦታ እንዲፈናቀሉና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረግ አግባብ አይደለም። ኢትዮጵያውያን  የሚታወቁት ዘር፣ ቀለም፣ ሐማኖትና ፖለቲካ ልዩነቶች ሳይከፋፍሏቸው ተከባብሮና ተዛዝኖ በመኖር ነው ያሉት ሐጂ ማሐሙድ ሁሉም በየእምነቱ ሰላምና የአገር አንድነትን ለማምጣት የሚካሔዱትን ተግባራት ሊያግዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የእስልምና ጉዳዮች የመስጅድና ኢቃፍ ዘርፍ መምሪያ ኃላፊ ሐጂ አብደላ ሰይድ እንደሚሉት፤ በእስልምና ሃይማኖት አስተምሕሮ መሰረት ሁሉም ሰው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብት ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰቡ በየእምነቱ ይቅር በመባባልና ያጠፉ ሰዎች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም