በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ውይይት በካርቱም እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ውይይት በካርቱም እየተካሄደ ነው
መስከረም 19/2012 በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ የተቋቋመው ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ስብሰባ በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም ማካሄድ ጀምሯል። በግድቡ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ የተቋቋመው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን 5ኛ ስብስባውን በካርም ማካሄድ መጀመሩን ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የጥናት ቡድኑ መስከረም 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ.ም በግብጽ ካይሮ በተደረገው ስብሰባ በሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት መስከረም 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም ካርቱም በሚካሄደው የሦስቱ ሀገራት ውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በአዲስ አበባ ተካሂዶ ከነበረው የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ወዲህ ድርድሩ ሳይካሄድ ቆይቷል። አዲሱ የሱዳን መንግስት ካቢኔ በቅርቡ መቋቋምን ተከትሎ ግን መስከረም 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ ም በካይሮ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን ግብጽ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ስብሰባ አድርገዋል። ይሁንና ግብጽ ባለፈው አንድ ዓመት ተቋርጦ የነበረው ድርድር በተለየ አካሄድ መቀጠል እንዳለበት በመግለፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ባቀረበችው አዲስ ምክረ ሀሳብ ላይ ውይይት እንዲደረግ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን ኢትዮጵያ ምክረ ሀሳቡን አልተቀበለችውም። ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ምክረ ሀሳብ የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እንዲሁም የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ የግድቡ ዋና ስራ ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚል ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ በካርቱም የሶስትዮሽ ስብሰባ ግድቡ ሳይንሳዊና አሳማኝ እንዲሁም የአገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ውሃ የሚሞላበትን መንገድ በምክረ ሀሳብ እንደምታቀርብ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሱዳንም የራሷን ምክረ ሀሳብ የምታቀርብ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታቀርበው ምክረ ሀሳብ ቀደም ሲል አቅርባው ከነበረው ብዙም የተለየ እንደማይሆንም ገልጸው ነበር። የሶስቱ አገሮች ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንስና የምርምር ኮሚቴ የህዳሴ ግድቡ እንዴትና በምን አይነት መንገድ ይሞላ፤ አሞላሉ በታችኛው ተፋሰሰስ አገሮች ላይ በተለይም በግድቦችና ሃይል ማመንጨት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚካሄድበትን ሁኔታ የሚያጠና ነው። የጥናት ቡድኑ ላለፉት 18 ወራት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች እያቀረበ ሲሆን ቡድኑ ከሶስቱም አገራት በተመሳሳይ አምስት ባለሙያዎች ተካተውበታል።