ቀጥታ፡

ጥንታዊ ፅሁፎችን ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ልማት መጠቀም ይገባል

መስከረም 19/2012 በኢትዮጵያ የሚገኙትን ጥንታዊ ፅሁፎች ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ልማት የእውቀት ምንጭ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳሰቡ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ትምህርት ክፍል ከሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ “ሂዮብ ሉዶልፍ ማዕከል” ጋር በመተባበር “የአትዮጵያውያና የኤርትራ ጥንታዊ ጽሑፎች ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ስልጠና  ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። አገሪቱ በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋዎች የተፃፉ በርካታ ጥንታዊ ፅሁፎች እንዳሏት ይነገራል። ሆኖም ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ጨምሮ በኪነ ጥበብ፣ ፍልስፍና ህክምና ዘርፎች ሀገር በቀል እውቀትን የያዙት ጥንታዊ ፅሁፎች ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ አለመሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናግረዋል። ይልቁንም ኢትዮጵያዊያን እነዚህን ጥንታዊ የእውቀት ምንጮች በመተው ትኩረታቸውን ወደውጭ ማድረጋቸውን አንስተዋል። በመሆኑም አገሪቱ ያሏትን አገር በቀል ዕውቀቶች የያዙትን ጥንታዊ ፅሁፎች በመፈተሽ ጥቅም ላይ እንዲውል ተመራማሪዎች ከዚህ በላይ እንዲሰሩ ሚኒስትሯ አሳስበዋል። ፅሁፎቹ የህክምና፣ የሠላም፣ የብልጽግናና የቴክኖሎጂ ዕውቀቶችን የያዙ የአገር ኃብት መሆናቸውን በመጠቆም። ሚኒስትሯ አክለውም፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች  ጠቅላይ ምክር ቤት እነዚህን ጥንታዊ ጽሁፎች ጠብቀው በማቆየታቸውና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል። ጽሁፎቹ የአገሪቱን "የትናንት መሠረት፣ የዛሬ ጉዞና የነገን መዳረሻ ለትውልዱ ማሳያ መስታወቶች ናቸው" ሲሉም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የፓትሪያርክ ጽ/ቤትና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም  በበኩላቸው  ስልጠናው አገር በቀል ዕውቀትን ለመጠቀም የሚያግዝ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ጥንታዊዎቹ ፅሁፎች የተጠቀሙባቸውን ቋንቋዎች ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ  ዕውቀቶቹን መጠቀም ይቻል ዘንድ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል። በዚህ ረገድ የጎንደር፣ የወሎ፣ የባህር ዳርና የማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሽ ናቸው። ለመጪዎቹ ሰባት ቀናት የሚቆየው ስልጠና በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋዎች የሚገኙ ጥንታዊ ጽሑፎች ዙሪያ አስፈላጊውን ባለሙያ ማፍራትና ዕውቀቱን መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኩራል። ጥንታዊ ፅሁፎች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ በሚችሉበት መንገድ ላይ መነጋገርም ሌላው ትኩረት ነው። ስልጠና የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ጀርመን የሚገኘው ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ  በተውጣቱ ምሁራን ነው። በስልጠናው ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርስ አጠባበቅ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።  ከተለያዩ አገራት የተጋበዙ የዘርፉ አዋቂዎችም የስልጠናው ተሳታፊ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም