ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰኔ 24 ጀምሮ ወደ ባርሴሎና በረራ ይጀምራል

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ሰኔ 24  2010 የስፔን ከተማ ባርሴሎና በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ። ወደ ከተማዋ የሚደረገው በረራ በቦይንግ በ787-800 ድሪምላይነር አውሮፕላን መሆኑን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ ክንፎቹን ወደ ባርሴሎና በማስፋቱ ከማድሪድ ቀጥሎ በስፔን ሁለተኛ መዳረሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የባርሴሎና ከተማ የአየር መንገዱ 13ኛ የአውሮፓ መዳረሻ ከተማ እንደሆነና በከተማዋ የሚደረገው በረራ የአየር መንገዱ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ የሆነው ራዕይ 2025 የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን የማስፋት እቅድ አካል እንደሆነም አስረድተዋል። ወደ ባርሴሎና የሚደረገው በረራ አዲስ አበባን ማዕከል በማድረግ በባርሴሎና ከተማ የሚገኙ የንግድ ሰዎችና ቱሪስቶች አየር መንገዱ ካለው 58 የአፍሪካ መዳረሻዎች ጋር እንዲተሳሰር የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል። ባርሴሎና የካታሎኒያ ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን በስፔን ከማድሪድ ቀጥሎ ብዙ ህዝብ የሚኖርባት ከተማ ነች። በተጨማሪም ከተማዋ በአውሮፓ ትልቅ የሚባሉ የንግድ ትርኢቶችና አውድ ርዕዮች ማዕከል ከሚባሉ ከተሞች ከሆላንድ አምስተርዳም ከተማ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓ 12ኛ መዳረሻ ወደ ሆነችው የስዊዘርላንድ ከተማ ጄኔቫ በረራ ግንቦት 30 ቀን 2010  በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። አየር መንገዱ በአምስት አህጉሮች 110 መዳረሻዎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም