የኢሬቻ በአል አዲስ አበባ መከበሩ መልካም እሴቱን ለማስፋት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በአል አዲስ አበባ መከበሩ መልካም እሴቱን ለማስፋት ያስችላል
ኢዜአ፤ መስከረም 17/2012 የኢሬቻ በአል የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መከበሩ የበአሉን መልካም እሴት ለማስፋት እንደሚያስችል የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
በኦሮሞ ባህል ከሰውም ሆነ ከፈጣሪ ለተደረገለት መልካምነት ምስጋናን ማቅረብ ከምንም በላይ መሆኑን የጠቀሱት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ በአሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣በፍቅርና በይቅርታ እንዲሳተፉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
“ኦሮሞ በዛፍም ሆነ በተራራ አያምንም፤ ከዚያ ይልቅ የፈጣሪ ድንቅ ስራዎች በሆኑት ውሀና ተራራ ላይ ምስጋና ለዋቃ ማቅረቡ ከባእድ አምልኮ ጋር አይገናኝም” በማለት ኢሬቻም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔን አጣምሮ መሄዱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣በፍቅርና በይቅርታ እንዲሳተፉ የሚያደርግ መሆኑንም ነው አቶ ከበደ የተናገሩት፡፡
በዚህ አመትም የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የአለም ታላላቅ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የኢሬቻ በአል መከበሩ መልካም እሴቱን ለማስፋት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ማንነትና ባህል ጠብቀዉ እንዳቆዩት ሁሉ ከሌሎች ጋር የሚጋሩትን እሴቶች በማጉላት ለብዝሀነትና ለአገር ግንባታ ማዋል እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የባህል ዘርፍ አጥኚ አቶ ስንታየሁ ቶላ ናቸው፡፡
አቶ ስንታየሁ እንዳሉት የኦሮሞ ህዝብ የኢሬቻን በዓል በተለያዩ ቦታዎች ለዘመናት ቢያከበርም ላለፉት ሁለት አስር ዓመታት ግን በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሀይቅ ከሌሎች ጋር በመሆን ስከበር ነበር፡፡
ኢሬቻና ሌሎች ሕዝባዊ በዓላት መከበር በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሻሻልም “ሁሉም ሰው የሌላውን ባህል ማዋቅና ማክበርን ይፈጥራል” ያሉት አባ ገዳ አብዱራዛቅ አብደላም ናቸው፡፡
የኢሬቻ በዓልን ማክበር አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመገንባትና ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ ያስችላል ያሉት አባ ገዳ አብዱራዛቅ፤ባለፉት ሁለት አመታትም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ተነሳሽነት በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ማክበራቸውን ገልጸው “ከአስራ ሁለት በላይ ብሄረሰቦች በቡድን ተደራጅተው በይፋ አክብረዋል” ብለዋል፡፡
በአሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪዝምን በማሳደግና ገጽታን በመገንባት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ኦሮሞ እንደማንኛውም ህዝብ የተለያየ እምነትና ፖለቲካ” ቢኖረውም ኢሬቻን ያለ ልዩነት ከኬሎች ህዝብ ጋር ማክበሩ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ትልቅ አቅም ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
“ቂም ተይዞ ኢሬፈና ማድረግ አይፈቀድም” ያሉት አቶ ከበደ፤ አባገዳዎች ባለፉት ሳምንታት ህዝቡ እንዲታረቅ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ሁሉም አካላት ከጸብ አጫሪ ድርጊትና ቃላት ተቆጥበው በአሉን በፍቅርና በአንድነት እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡