የመስቀል በዓል የአብሮነትና የአንድነት ተምሣሌት በመሆኑ ሁሉም ሊጠበቀው ይገባል - አምባሳደሮችና ቱሪስቶች - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል የአብሮነትና የአንድነት ተምሣሌት በመሆኑ ሁሉም ሊጠበቀው ይገባል - አምባሳደሮችና ቱሪስቶች
መስከረም 17/2012 የመስቀል ደመራ በዓል የሕዝቦች የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች የሚጠናከሩበት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀው እንደሚገባ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና የውጭ አገር ቱሪስቶች ገለጹ። የመስቀል ደመራ በዓል እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከተደበቀበት ስፍራ መገኘትን በማስመልከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች በየዓመቱ መሰከረም 17 ይከበራል። ከስድስት ዓመታት በፊት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር የዓለም ቅርስ አድርጎ መዝግቦታል። የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶችም የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ የሆነውን የመስቀል በዓል ያከብራሉ። በዓሉን የታደሙት በኢትዮጵያ የሰርቢያ አምባሳደር አሌክሳንደር ሲስቲክ እንደተናገሩት በዓሉ የኦርቶዶክስ አማኞችን ብቻ ሳይሆን የሌላ እምነተ ተከታይንም ቀልብ የሚስብ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የዓለም ቅርስ የሆኑ የቱሪዝም ኃብቶች እንዳሏት ገልጸው ይህም አገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም እንደሚያሳይ ተናግረዋል። በመሆኑም የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ በመሆኑ ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጌ ደግሞ በዓሉን መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቀጣይ ዓመታትም እንደዚህ በድምቀት መከበር አለበት ብለዋል። የበዓሉ ታዳሚዎች የነበሩት የውጭ አገር ቱሪስቶችም በዓሉ እንዳስደሰታቸውና የአብሮነት፣ የአንድነትና የሠላም ተምሳሌት መሆኑን ጠቁመዋል። ከካናዳ የመጡት ጉብኚ ትሪሻኬንጋ መስቀልን ለማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልጸው በዓሉ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአንድ ዓላማ መሰባሰባቸው ከፍተኛ አግራሞት እንዳጫረባቸውም ነው ያነሱት። በርካታ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ መምጣታቸው በራሱ የመስቀል በዓል የሠላምና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። እንግሊዛዊው ብሬህ ማይናርድ ደግሞ መስቀልን ለማክበር ከሃያ ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣና የአሁኑ ሁለተኛ ጊዜያቸው መሆኑን ነው የተናገሩት። የመስቀልን በዓል የኃይማኖቱ ተከታዮችና ሌሎችም በአንድነት መጥተው ማክበራቸው እይታን እንደሚማርክ ገልጸዋል። የኃይማኖቱ ተከታዮችም በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ሥፍራዎች በዝማሬና በኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ታጅበው በመስቀል አደባባይ በሠላም ማክበራቸው ይማርካል ብለዋል። ቤተ-ክርስቲያኗም የበዓሉን አከባበር በሚገባ ሰንዳ ለዓለም በማስተዋወቅ በሥፍራው መገኘት ያልቻሉትን እንዲያዩ ማድረግ አለባት ሲሉም ምክረ ኃሳብ ሰጥተዋል። ከአሜሪካ የመጣው ሚራንዳ ቤክ ማን ደግሞ በበዓሉ ላይ በመገኘቱ የተሰማውን ደስታ ገልጾ በዓሉ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ በመሆኑ በርካታ ሰዎችን ማቅረብ ችሏል ብሏል። የመስቀል ደመራ ክብረ-በዓል በኢትዮጵያ ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ሲከበር ቆይቷል።