ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያን የህዝቦችን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ለሰላም መረጋገጥ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተገለጸ

መስከረም  17/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በህዝቦች መካከል ያለውን የአንድነትና የአብሮነት እሴት በማጠናከር ለሀገሪቱ ሰላም መስፈን የበኩሏን እንደምትወጣ የጋምቤላ፡የአሶሳ፡የምዕራብ ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳሳት አስታወቁ፡፡ በጋምቤላ ከተማ የደመራ በዓል የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት በድምቀት ተከብሯል፡፡ የአህጉረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በህዝቦች መካከል የቆየውን አንድነት በማጠናከር ለአገሪቱ ሰላም የምታበረክተውን እስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡ ምዕመነናኑም አባቶች ያቆዩትን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ለአገሪቱ ሰላምና እድገት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችን በሰከነ መልኩ በመመልከት ህዝበ ክርስቲያኑ ሰላሙን እንዲያስጠበቅ አሳስበዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለውን ሰላም እና አንድነት ለማስቀጠል ሁሉም በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ቤተክርስቲያኗ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ እየተካሄደ ላለው ሰላምና አንድነት ግንባታ እያበረከተችው ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡   በቀጣይም ይህንኑ መልካም ተግባሯን አጠናክራ በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የድርሻዋን እንድትወጣ ጠይቀዋል፡፡   ቤተክርስቲያኗ ለምታካሄዳቸው መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንባታ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም