ቀጥታ፡

የመሰባሰብና መደመር ምልክት ከሆነው የመስቀል በዓል ፍቅርና ይቅርታን ልንማር ይገባል

መስከረም  17/2012 የኢትዮጵያዊያን የመሰባሰብና መደመር ምልክት ከሆነው የመስቀል በዓል ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነትን መማር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶችና መዕመናን ገለጹ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ መስቀል የጥላቻ ግንብ ማፍረሻ የተጣሉ መታረቂያ፣ የመዳንና የመተሳሰብ በዓል ነው። ኢትዮጵያዊያን በተለይም የእምነቱ ተከታዮች "ከጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የመከራ ደብዳቤያችን የተቀደደበትና ከጥፋት የዳንንበት ነው" በሚል በድምቀት ያከብሩታል። የመስቀል ደመራ በዓል ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ መላው ኢትዮጵያዊያንና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ ዜጎችም በጋራ ያከብሩታል። በዓሉ ትናንት በመስቀል አደባባይ ሲከበር ምዕምናን ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለያያቸው በራሳቸው ልሳን መስቀል ኃይላችን፣ መዳኛችን፣ መሰባሰቢያችን ሲሉ ዘምረዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ መልከ ጸዴቅ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መስቀል የሠላም፣ የአንድነትና የመሰባሰብ በዓል ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ጥላቻና ክፉ ነገርን ከልባቸው በማውጣት በፍቅርና በትብብር ሊያከብሩት ይገባል ብለዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ መስቀል መንፈሳዊና ማህበራዊ ይዘት ያለው የአንድነትና የሠላም በዓል መሆኑን ገልጸዋል። መስቀል ብዙ በመሆን እንደ አንድ የሚከበር የአንድነት የአብሮነትና የትብብር እንዲሁም ለኢትዮጵያዊያን የማንነት መገለጫ ነው ብለዋል። የደብረ ምጥማቅ ሳሊተ ምህረት ሊቀ ጠበብት ፍቅረ ዮሐንስ አስፋው ደግሞ እምነትና ተስፋ ጸንተው ይኖራሉ፤ ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል ይላሉ። የመስቀል ደመራ በዓል 'ኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚያከብሩት፤ በኢትዮጵያዊያን ባለቤትነት የዓለም ቅርስ የሆነ ነው' ብለዋል። የጽርዓ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ዲያቆን ደረጄ ጌታው መስቀል የሰላም በዓል መሆኑን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ተሰቅሎ እንዳዳነን፣ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም የይቅርታና የአንድነት ልብ ሊኖረን ይገባል ሲሉም መክረዋል። የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚያከብሩት፤ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም