የደመራ በዓል የቤተክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ቅርስ በመሆኑ በጋራ ሊጠበቅ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የደመራ በዓል የቤተክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ቅርስ በመሆኑ በጋራ ሊጠበቅ ይገባል
መስከረም 17/2012 የመስቀል ደመራ በዓል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ሕዝብ ቅርስ በመሆኑ በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ጠየቁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የሚከበረው መንፈሳዊ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ የሩሲያና የግብጽ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የውጭ አገር መገናኛ ብዙሃንና ጎብኚዎች ታድመዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የደመራና መስቀል በዓል ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ የመላው ዓለም የጋራ ሃብት ሆኗል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል 'የኢትዮጵያዊያን ኩራትና የማንነታችን መገለጫ ነው' ብለዋል። የመስቀል ደመራ በዓል ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ባለፈ የመላው ኢትዮጵያዊያን በዓል በመሆኑም በጋራ ልንጠብቀው ይገባል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ መምህር ዕንቁባህርይ ተከስተ ደግሞ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶቹ የኢትዮጵያዊያን የሆነውን በዓል መሰረቱን ሳይለቅ ለዓለም ለማስተዋወቅ ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለይ በጋራ መንከባከብ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። መምህር በቃሉ ሞላ የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ካህን ቀሲስ ፋሲል ታደሰ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን ስርጭት ክፍል አገልጋይ፡- የወንጌል መምህር የሆኑት መምህር ላቀው አክሊሉም "እኛ ጠብቀን ከዚህ አድርሰናችኋል ቀጣዩ መንገድ ደግሞ የእናንተ የወጣቶች ነው" የሚል መልዕክት አስተላለፈዋል። ታሪክን መሰነድ፣ መጠበቅ፣ መንከባከብና ለትውልድ ማስተላለፍ የወጣቱ ትውልድ የጋራ ስራ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።