ቀጥታ፡

ጋዜጠኞች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል

መስከረም  17/2012 የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ለጋዜጠኞች ያዘጋጀው ስልጠና ተጠናቋል። በአልጀዚራ ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠና ጋዜጠኞች በሥራ ላይ ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ራሳቸውን መጠበቅ የሚያስችላቸውን ክህሎት ያስጨበጠ ነው ተብሏል። በስልጠናው ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ የግልና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን እንደዚሁም አዲስ አበባን ጨምሮ የጎረቤት አገራት የአልጀዚራ ቢሮ ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል። ላለፉት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ የተሰጠው ስልጠና ጦርነትን፣ ግጭትን፣ ረብሻ የተቀላቀለበት ህዝባዊ ሰልፍና ሌሎች ጥንቃቄ የሚሹ ሁነቶችን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ህይወታቸውን ከአደጋ በመጠቀብ ሥራቸውን መከወን በሚችሉበት ክህሎት ላይ ያተኮረ ነው። ሠላምና መረጋጋት በሌለባቸው አካባቢዎች በጋዜጠኞች ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ እገታና ዝርፊያን የመሳሰሉ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የሚያግዝ ክህሎትም የስልጠናው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ስልጠናው ሲጠናቀቅ ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት የሰጡት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት ጋዜጠኞች በተለይ መስክ ላይ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች ሊገጥሟቸው ይችላሉ። በመሆኑም በአገር ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ የሚዲያ ተቋም ለጋዜጠኞቹ ደህንነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። በተለይ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ምክንያት ሊደርስባቸው የሚችለውን የአካልና የህይወት አደጋ ለመከላከል ጋዜጠኞች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። እናም ጋዜጠኞች ወደ መስክ በሚሰማሩበት ወቅት አስፈላጊውን የህይወት አድን ጥንቃቄ የማድረግ ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል፤ የመጀመሪያ ህክምና መርጃን ጨምሮ ተያያዥ ቁሳቁሶምች ማደራጀትም ያስፈልጋን ብለዋል። በርካታ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች የሚሳተፉበት ተመሳሳይ ስልጠና የሚዘጋጅ መሆኑንም ዶክተር ጌታቸው አረጋግጠዋል። በዚህ ረገድ ከአልጀዚራ ጋር ያለው የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በኳታር የአልጀዚራ የፐብሊክ ሊበርቲስና ሂዩማን ራይትስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር መሐመድ አልፋሪሲ ጋዜጠኞች ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በቅድሚያ ደህንነታቸው ሲጠበቅ ነው ብለዋል። "ሚዲያዎችም ከሚቀርበው ዘገባ ይልቅ ለጋዜጠኞች ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የአልጀዚራ መመሪያም ይኸው ነው ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰማርተው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተጋለጡ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን እንደሚለው በአውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር 2018 እንኳ 94 ጋዜጠኞች በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል። እነዚህ የሚዲያ ሰዎች የሞቱት ሆን ተብሎ በተፈጸመባቸው ግድያ፣ በቦንብ ፍንዳታና በተፋላሚዎች መካከል በሚካሄድ የተኩስ ልውውጥ በጥይት ተመትተው መሆኑንም አመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም