ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 16/2012 የደመራን በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ አገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጎብኚዎች፣ እንግዶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ታድመውበታል። የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን፤ መስቀል ደግሞ በማግስቱ መስከረም 17 ቀን ይከበራል። እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በዓሉ በመስቀል አደባባይ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ከተከወኑ በኋላ ደመራው ተለኩሷል። ከተከናወኑት መርሃ ግብሮች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የሃይማኖት አባቶችና የመዲናዋ ከንቲባ ተወካይ ያደረጉት ንግግር ይጠቀሳሉ። ብፁእነታቸው "ነገረ መስቀሉ የተለያዩትን አሰባስቦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ የተጣሉትን አስታርቆ በአንድ መዓድ የሚያቀርብ ነው" ካሉ በኋላ ሁሉም ሠላሙንና አንድነቱን በጋራ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል። እርስ በእርስ በመዋደድና በመከባበር አባቶች ያስረከቡትን አገር "በጋራ መጠበቅ ያስፈልጋል" ያሉት አቡነ ማትያስ ዛሬ የጎደለውን ሠላም፣ ፍቅርና አንድነት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ድርሳናት እንደሚያስረዱት የደመራ በዓል እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ለዘመናት ከተደበቀበት ስፍራ የተገኘበት ዕለት ነው። ትውፊቱ እደሚለው የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች። ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜም መስቀሉ ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ስፍራ የሚያሳያት አጥታ በፍለጋ ብዙ ጊዜ አሳለፈች። በኋላ ግን ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን በማጤስ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን መስቀሉ የተቀበረበትን ሥፍራ ጢሱ አመላከታት። መስከረም 16 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት 10 መስቀሉ ተገኝቷል፤ አብረው ከተገኙ ሌሎች መስቀሎች የእየሱሰ ክርስቶስ መስቀል ተዓምር በማድረግ ይለይ ነበር ይላሉ የቤተ-ክርስቲያኗ ድርሳናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ይህን መሰረት በማድረግ ከ1600 ዓመታት በላይ የመስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ ዕለቱን እያከበረችው ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ የንግስቲቱን ተግባር አብነት በማድረግ የቤተ-እምነቱ አማኞች በተለያዩ ሥፍራዎች ደመራ በመደመርና በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ያከብሩታል። ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግዕዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግዕዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም የመስቀል በዓል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል። የመስቀል ደመራን በዓል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር የዓለም ቅርስ አድርጎ መዝግቦታል። በኢትዮጵያ በየዓመቱ በርካታ የውጭ አገር ጎብኚዎች ከሚጎበኟቸው ኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች መካከል የመስቀል ደመራ በዓል ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም