"አንድነታችንንና ሰላማችንን የጋራ ሃብት አድርገን እንጠብቅ" - ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
"አንድነታችንንና ሰላማችንን የጋራ ሃብት አድርገን እንጠብቅ" - ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 16/2012 "አንድነታችንንና ሰላማችንን የጋራ ሃብት አድርገን እንጠብቅ" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስገነዘቡ። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የደመራ በዓል ስነ ስርዓት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስ ባሰሙት ንግግር አጽንኦት የሰጡት ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመፍጠርና በመደጋገፍ በጋራ መጠቀም አለባቸው። ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በመስቀል አደባባይ የደመራ በዓል በልዩ ስነ ስርዓት እያከበሩ ናቸው። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንደሚገልጹት ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ለብዙ ዘመናት ተቀብሮ ከቆየበት ስፍራ በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ተገኝቷል። ለዘመናት ተቀብሮ ከኖረበት በቁፋሮ የወጣው መስቀል ፍቅር፣ ሰላምና ዕርቅ የተገለጠበት ነው። "ነገረ መስቀሉ የተለያዩትን አሰባስቦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ የተጣሉትን አስታርቆ በአንድ መዓድ የሚያቀርብ ነው" ያሉት ፓትሪያርኩ፤ ሁሉም ሰላሙንና አንድነቱን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። እርስ በርስ በመዋደድና በመከባበር የአባቶች ያስረከቡትን አገር "በጋራ መጠበቅ ያስፈልጋል" ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ዛሬ የጎደለውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ፓትርያርኩ አያይዘውም "ቤተ ክርስቲያንን እየደፈሩና እየዘረፉ ሰላምንና አንድነትን ማምጣት አይቻልም። ይህ አጥፊ ድርጊት መሆኑ ታውቆ ባስቸኳይ መቆም አለበት፣ እስከመጨረሻውም መገታት አለበት" ብለዋል። አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች ሆኑ ሌሎች አካላት ህዝብን ከመነጣጠል አብሮነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በማስቀደም ተግተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ከ1 ሺ 600 ዓመታት በላይ የመስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ ዕለቱን እያከበረችው ትገኛለች።